የዓለም ሀገራትን ኢኮኖሚ መዝኖ ደረጃ የሚሰጠው ተቋም ፊች ለኢትዮጵያ ዝቅተኛ ደረጃ ሰጠ። ሀገሪቱ ከፍተኛ የብድር ጫና ያለባት መሆኗ እና የዋጋ ንረቱ ማየል ለዝቀተኛ ደረጃ ማግኘቷ በምክንያትነት ተጠቅሷል ።
ሀገሪቱ ያገኘችው ሲ ደረጃ ኢትዮጵያ በኢንቨስተሮች ዓይን ዝቅተኛ ግምት እንዲሰጣት ያደርጋል ተብሏል።
የሀገራትን ኢኮኖሚ መዝኖ ደረጃ የሚሰጠው እና የአሜሪካ እና እንግሊዝ መሰረት ያለው ፊች ለሀገራችን ዝቅተኛ የተባለውን ደረጃ ሰጥቷል።
ተቋሙ በመጨረሻው ሪፖርቱ ሀገራችን ያለባትን የብድር ጫና እና በጦርነት የተዳከመ ኢኮኖሚዋ ጋር በተያያዘ አስቀድሞ ሰጥቷት ከነበረው ደረጃ ቢ የሲ ደረጃን ሰጥቷታል።
የደረጃ ሰጭ ተቋሙ ለሀገራችን የሰጣት ደረጃ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር ጫና እንዳለባት የሚያሳይ ነው። ተቋሙ በዚህኛው በጄት ዓመት 1.6 ቢሊዮን ዶላር ብድር መከፈል ይጠበቅባታል ያለ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ደግሞ 1 ቢሊዮን ዶላር ብድር መክፈል ይጠበቅባታል ብሏል። ይሁንና ግን ዓለም አቀፍ ተቀማጯ ወደ 1.5 ቢሊዮን ዶላር አሽቆልቁሏል ብሏል።
የሀገራት የብድር ጫና ውስጥ መሆን፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን የመሳብ አቅም መዳከም፣ የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት፣ የበጄት ጉድለት ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ የሚያደርጉ ሲሆን ሀገራችንም በነዚህ መመዘኛዎች ዝቅተኛ ደረጃ ተሰጥቷታል።
የዚሁ ተቋም መረጃን አለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ተቋማት እንደዋቢ የሚጠቀሙት መሆኑ ደግሞ በሀገራችን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ሊኖር የሚችለው ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም።
ኢትዮጵያ የነበሩባትን ዕዳዎች እንዳታቀል የሰሜኑ ጦርነት የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረውም የሚጠቀስ ነው።
ተቋሙ በሌላ በኩል በፌደራል መንግስት እና ህወኃት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጨቱ የመካከለኛ እና ማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፉን ብሎም የዓለም አቀፍ የአቅርቦት መስተጓጎሉን እንዲሻሻል በማድረግ ያለችበት ደረጃዋ እንዲሻሻል ሊያግዛት ይችላል ብሏል።
ከኬንያ በመቀጠል የምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚን የምታንቀሳቅሰው ሀገራችን የነበሩባትን ዕዳዎች በቡድን 20 ዕዳ የመቀነስ የጋራ ተነሳሽነት ማዕቀፍ በኩል የብድር ሁኔታዋ እንደገና እንዲዋቀር እና ጫናዋ እንዲቀልላት ሂደቶችን ባሳለፍነው ዓመት ጀምራ የነበረ ቢሆንም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከስምምነት ላይ ሳይደረስ ተጓቷል።
እንደ አይኤም ኤፍ እና የዓለም ባንክ ያሉ የገንዘብ ተቋማት ጋር እያደረገች ያለችው ጥሩ ግንኙነት የተሻለ የብድር ጫናዋን እና የገንዘብ ችግሯን ያቃልላል የሚል ግምት እንዳለውም አስቀምጧል።
በአብርሃም በለጠ
2022-12-21
