ሀገሬ ቲቪ

45 ዲግሪ ያዘነበለው ቤተ-መቅደስ

የሩቅ ምስራቅቆቹ ኤዢያውያን አብዝተው በተፈጥሮ አደጋዎች አበሳቸውን የሚያዩ ዜጎች ናቸው። የመሬት መንቀትቀጥ፣ የመሬት መንሸራተት እና ሱናሜ ደጋግመው ይጎበኟቸዋል።

ታዲያ ከእነዚህ ሀገራት መካከል ታይዋን አንዷ ናት። ታይዋን በነሐሴ 2001 ዓ.ም. ሞራኮት በተባለ ከባድ ዝናብ በቀላቀለ አውሎ ነፋስ ትመታለች።

ይህ አውሎ ነፋስ በታይዋን ታሪክ ከባድ ከተባሉት መሀከል የተመዘገበም ነበር። በግዜው 673 ሰዎችን ለሞት ሲዳርግ በቁስ ላይም ያደረሰው ጉዳት 3.3 ቢሊዮን ያህል እንደነበር ተመዝግቧል።

ታዲያ በዚህ አውሎ ነፋስ በርካታ ዜጎቿን እና ሀብቷን ያጣችው ታይዋን አደጋው አንድ ሲሳይን ሰጥቷት ነው ያለፈው።

አውሎ ነፋሱ ያስከተለው የመሬት መንሸራተት የታይሄ ዠንሲንግ ቤተ መቅደስ 45 ዲግሪ እንዲያዘነብል አድርጎታል። በዙህም ሳቢያ ቦታው የበርካቶችን ትኩረት መሳብ ችሏል።

ከ2001ዱ አደጋ በፊት ቀት ብሎ ቆሞ የነበረው ቤተመቅደሱ የደረሰው አደጋ ከነበረበት 45 ዲግሪ ያህል ወደ ጎን ዘመም እንዲል አድርጎታል።

በተለይ አሁን የአካባቢው ጎብኚዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በሚለቋቸው ፎቶዎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ይበልጥ እያስተዋወቁት ነው።

በዚሁ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሳቢያ ከእስከዛሬው ከፍ ያለ ገቢን እያስገኘ መሆኑን የሀገሬው መገናኛ ዘዴዎች ተናግረዋል።

በርካቶችም በጣሊያን ካለው የፒሳ ዘንበል ያለ ግንብ የበለጠ ሳቢ ነው እያሉለትም ይገኛሉ።

በሳምሶን ገድሉ
2022-12-26