ሀገሬ ቲቪ

የኩፍኝ ወረርሽኝ መስፋፋት ምክንያት

በኢትዮጲያ ባሉት ጦርነቶች ምክኒያት ያልተከተቡ ህፃናት ቁጥር መጨመር ለኩፍኝ ወረርሽኝ መስፋፋት መንስኤ መሆኑ ተገለፀ።

ወረርሽኙ በቀላሉ በንክኪ የሚተላለፍ ሲሆን በሽታው ከአምስት አመት በታች ያሉ ህፃናትን ያጠቃል። ወረርሽኙን ልመግታትም 95 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት ክትባት መከተብ ሲችሉ መሆኑ ተገልጿል።

በአለም ላይ በክትባት ብቻ መከላከል እና መቆጣጠር ከሚቻሉ በሽታዎች መካከል ኩፍኝ አንዱ ነው።

ኢትዮጵያም የኩፍኝ በሽታን ከሱማሌ ክልል በስተቀር በክትባት ዘመቻዎች እንዲሁምም በመደበኛ የክትባት መርሃ ግብሮች መቆጣጠር ችላ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ሰአት ላይ ደግሞ በሽታው እንደ አዲስ በወረርሽኝ መልክ እየተስፋፋ መቷል።

ወረርሽኙ በሃገር አቀፍ ደረጃ መስፋፋቱ ምን ይሆን ብለን በጤና ሚኒስተር የክትባት ባለሙያ የሆኑትን አቶ ሃብታሙን አናግረናል፡፡

የህፃናተን ሞት ከሚያስከትሉ በሽታዎች መካከል ኩፍኝ አንዱ ሲሆን 10 በመቶ የሚሆነው የህፃናት ሞትም የሚከሰተው በዚሁ በሽታ ነው።

የኩፍኝ በሽታ በቀላሉ ከሰው ወደሰው የሚተላለፍ ነው ያሉን በዘውዲቱ ሆስፒታል ጠቅላላ ሃኪም የሆኑት ዶ/ር አመንቲ የበሽታው ምልክቶች ደግሞ ብዙ ጊዜ ሰዎችን ያዘናጋሉ ብለውናል።

ይህ መድሃኒት ያልተገኘለት በሽታ ብዙን ጊዜ ህፃናት በሽታን የመከላከል አቅማቸው ሲደክም የመያዝ አቅማቸው ከፍተኛ ነው።

ዶ/ር አመንቲ በበሽታው የተያዘ ህፃን ቶሎ ወደ ህክምና ማዕከላት ቢሄድ በጤና ባላሙያዎች በሚደረግለት እገዛ እና ክትትል የከፋ ጉዳት ሳይደርስበት ይድናል ብለዋል።

የኩፍኝ በሽታን መከላከል የሚቻለው ህፃናቶች በዘጠኝ ወራቸው እና በአንድ አመት ከሶስት ወራቸው በሚወስዷቸው የኩፍኝ መከላከያ ክትባቶች የበሽታ መከላከል አቅማቸው ሲያድግ እንዲሁም በሃገር አቀር ደረጃ 95 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት የኩፍኘ መከላከያ ክትባት መውሰድ ሲችሉ መሆኑ ተገልጿል።

በማህሌት አማረ
2022-12-27