ሀገሬ ቲቪ

ሰሜን ኮሪያ የመከላከያም፣ የኢኮኖሚም አቅሜ አድጓል አለች

የሰሜን ኮሪያ የባህል፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የመከላከያ ሃይል አቅሟ ማደጉን የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን በሰራተኞች ፓርቲ አመታዊ ስብሰባ ላይ ገልፀዋል።

የተጣሉባትን ማዕቀቦችንም መቋቋም ችላለች ተብሏል። ከሰሞኑ ለሩሲያም ድጋፍ አድርጋለች እየተባለች የምትወቀሰው ሰሜን ኮሪያ በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ማዕቀቦችን ከምዕራቡ አለም አስተናግዳለች፡፡

ብዙ ጊዜም ኢኮኖሚዋ ተጎድቷል የሚሉ ዜናዎችም መውጣታቸው አይዘነጋም። ነገር ግን የተጣሉብኝ ማዕቀቦችም ሆኑ ከፊቴ የተጋረጡት ፈተናዎች የበለጠ አጠንክረውኛል እያለች ትገኛለች፡፡

ሰሜን ኮሪያ የ2023 እቅዷን ይፋ በምታደርግበት እና የ2022 ጉዞዋን በምትቃኝበት በሰራተኞች ፓርቲ አመታዊ ስብሰባን በከፈቱበት ወቅት የሃገሪቱ ፕሬዝዳት ኪም ጆንግ ኡን ሃገራቸው በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እንዲሁም በወታደራዊ አቅሟ የተሻለ እድገት ማሳየቷን ተናግረዋል።

ኪም ጆንግ በ2022 ሃገራቸው ትልልቅ ተግባራትን ያከናዎነችበት እና ያልተጠበቁ ፈተናዎችን የተጋፈጠችበት መሆኑንም አልሸሸጉም።

ነገር ግን የኢኮኖሚ ተንታኞች ደግሞ ሰሜን ኮሪያ በማዕቀብ አለንጋ እየተገረፈች ምጣኔ ሃብቷም ኪም ከጠቀሱት በተቃራኒው እየተዳከመ ስለመሆኑ ያነሳሉ።

ከሚጣልባት ተከታታይ ማዕቀቦች በተጨማሪ ደግሞ የኮሮና ወረርሽኝ እና የተፈጠሮ አደጋዎችም ለትንሿ ሀገር ዜጎች ፈተናውን አክብዶባቸዋል ነው የሚባለው።

ሰሜን ኮሪያ በ2023 በብረት፣ ኬሚካል፣ ኤሌክትሪክ፣ ግንባታ እና ግብርና ዘርፎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ኪም መግለጻቸውን የሃገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

በጦር መሳሪያ ሃያላን ከሚባሉት ሃገራት ተርታ የምትሰለፈው ሰሜን ኮሪያ እየተገባደደ ባለው 2022 ከ60 በላይ የባልስቲክ ሚሳይሎችን የሞከረችው ሰሜን ኮሪያ ከጎረቤቶቿ እና አሜሪካ ጋር ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብታ ከርማለች፡፡

አሜሪካ ለደቡብ ኮሪያ ኒዩክሌር እስከማስታጠቅ የደረስ ድጋፍ አደርጋለሁ ማለቷ የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን አባብሶት ሰነብቷል። በተላንትናው እለትም ሰሜን ኮሪያ አምስት ድሮኖች የደቡብ ኮሪያን የአየር ክልል ጥሰው ምብረራቸው ሴኡል ተዋጊ ጄቶቿን እና ሄሊኮፕተሮቿን እንድታሰማራ አስገድዷል ተብሏል።

በማህሌት አማረ
2022-12-27