ሀገሬ ቲቪ

ለግብርና ሲል የፋይናንስ ስራውን የተወው ቻይናዊ ስራ ፈጠሪ

ከልብ የወደዱትን፤ ውስጦ የሚሻውን ሰርቶ መኖር በርካቶች ይመኙታል። አንዳንድ ልባሞች ግን የምኞታቸውን ዓለም በእውን ይኖሩታል። ይህ ቻይናዊም የዚሁ ተግባር ምሳሌ ነው።

ከ14 ዓመታት በፊት አትራፊ የነበረውን የፋይናንስ ስራውን እርግፍ አድርጎ ትቶ ወደ ግብርናው ፊቱን ያዞረው የ39 ዓመቱ ሁአንግ ዜን አሁን በርካቶችን አጀብ አሰኝቷል።

የበርካቶች መገረም ምክንያት ደግሞ የዚሁ ገበሬ የፈጠራ ውቴት የሆነው ቴክኖሎጂ ነው።

ሁአንግ በምስራቅ ቻይና የፖለቲካ፣ ሳይንስ እና ህግ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላ ወደ ፋይናንሱ ዓለም ተቀላቀለ። ብዙም ሳይቆይ የፋይናንሱ ዓለም ለእሱ እንደማይሆንለት ተረዳ፤ ግዜም አላጠፋም ስራውን እርግፍ አድርጎ ተወው።

ስራውን አቋርጦ በሻንጋይ ቾንግሚንግ ደሴት ከወላጆቹ ጋር ተፈጥሯዊ አትክልቶችን የሚያመርትበት 121 ሄክታር መሬት አገኘ።

ሁአንግ ባህላዊውን ከዘመናዊው የግብርና ዘዴዎች ጋር እያጣመረ በግብርናው እየተዋጣለት መጣ። ታዲያ ያኔ የፍየሎች በውልደታቸው ግዜ መሞት አሳሰበው፤ አንድ ነገርን አሰበ እና አደረገው።

ቴክኖሎጂው ፍየሎች በሚወልዱበት ግዜ በሚከሰት አደጋ ይፈተር የነበረውን የግልገሎች ሞትን የሚያስቀር ነው ተብሎለታል።

ፍየሎች በሚወልዱበት ግዜ ገበሬዎች ይከተሉት የነበረው ዘዴ ከ5 እስከ6 ከመቶ ክረምቱ ሲገባ ደግሞ ወደ 10 በመቶ ግልገሎች እንዲሞቱ የሚያደርግ ነው።

ታዲያ ይህ ቴክኖሎጂ በኤ አይ ቴክኖሎጂ የሚታገዘው ፈጠራው ፍየሎቹ በሚወልዱበት ግዜ በአካባቢው ላሉ የግብርና ሰራተኞች መልዕክትን ያደርሳል።

የተለየ ችግር ባጋጠመ ግዜ የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች እርዳታ እንዲያደርጉም የሚያግዝ ነው።

ቴክኖሎጂው በጋጣ ውስጥ በተገጠመ ካሜራ አማካኝነት አርተፊሳል ኢተለጀንስን በመጠቀም በመውለድ ላይ ያለችዋን ፍየል ለይቶ ማሳወቅ የሚችል ነው።

የቀድሞ የፋይናንስ ባለሙያው ሰው አሁን የ2 ሺሕ ፍየሎች ባለቤት ነው፤ እነዚህ ፍየሎች ታዲያ በመውለጃ እድሜ ላይ የሚገኙ ናቸው።

ታዲያ በአዲሱ ቴክኖሎጂ በመታገዝም 600 የፍየል ግልገሎችን ከሞት መታደግ መቻሉንም ይናገራል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-12-27