ሀገሬ ቲቪ

የተማሪዎች አመጽን እንደገና ያፋፋመው ግድያ

በዘመነ ኃይለ ሥላሴ በመጧጧፍ ላይ የነበረው የተማሪዎች አመጽ ቀዝቀዝ ማለት አሳይቶ ነበር። ይሁንና ከ53 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ሊቀመንበር የነበረው ጥላሁን ግዛው ከ53 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት መገደሉ የተማሪዎች አመጹን እንደገና እንዲፋፋም አድርጎታል።

በዘመነ ኃይለ ሥላሴ ተማሪዎች መሬት ላራሹ የሚል አመጽን በንጉሱ አስተዳደር ላይ ጀምረዋል። በጊዜው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት በነበረው በዚህ አመጽ የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ሊቀ መንበር የነበረው ጥላሁን ግዛው የዚህ እንቅስቃሴ ዋነኛ ተዋናይ ነበር።

ለጥላሁን በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ቢደርሱትም እርሱ ግን ከእንቅስቃሴው መሪነቱ አላፈገፈገም ነበር። ይሄው የ29 ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በአዲስ አበባ አፍንጮ በር አካባቢ ታህሳስ 19/1962 ዓ.ም. ከወንድሙ እና ከጓደኛው ዮዲት ጋር በቆመበት ታርጋ ከሌላት መኪና ውስጥ በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ አልፋለች።

ይሄው የጥላሁን ግዛው ግድያ የተማሪዎችን ቁጣ ቀስቅሶ የተማሪዎች አመጽ እንደገና እንዲፋፋምም ምክንያት ሆኗል።

“እስከዛሬ ድረስ ልቤ ሲከዳኝ ፤
ተምሮ ጥላሁን ሞት አስተማረኝ ፤
እንግዲህ አልፈራም አልጓጓም ለነፍሴ ፤
ቦታ አግኝቻለሁኝ ጥላ ለፈረሴ ፤
አንተ ጋር ገስግሷል ጥላሁን መንፈሴ።”
የሚል ስንኝም ተቋጥሮለታል።

ጥላሁን ግዛው ከንቡረዕድ ግዛው አበራና ከእናቱ ከወይዘሮ ደሴ አደዬ ረታ በ1933 ዓ.ም በራያና ቆቦ አጠርሻ በመባል በምትታወቅ የገጠር መንደር ነው የተወለደው። የቤተክህነት ትምህርቱን እስከ ዳዊት ተከታትሏል።

ቀጥሎም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ወልድያ ጣይቱ ብጡል ትምህርት ቤት ጀምሯል። በአሥራዎቹ መጀመሪያ ዕድሜው ከአባቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እንጦጦ ሚሽን አዳሪ ትምህርት ቤት የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቋል።

በማስከተልም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሎ በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ በ1959 ዓ.ም የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀላቀለ።

ቀድሞም የመሬት ላራሹ ስሜት እንደነበረው የሚነገርለት እና ገና የሁለተኛ ደርጃ ተማሪ እያለ በመሬት ላራሹ ሰልፎች ላይ የሚሳተፈው ወጣቱ ጥላሁን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በነበረው የንጉሱ እና ባላባቱ ስርዓት ተቃውሞ ላይ ዋነኛ መሪ ሆኗል።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ውስጥ ለውስጥ ተማሪውን የሚቀሰቅስ ‘’አዞዎቹ ‘’ የተሰኘ ቡድንም አባል ነበር። ኋላም በግልጽ ተቃውሞም ቢሆን ግንባር ቀደም ነበር።

ውልደቱ ከባላባቱ ወገን ቢሆንም ውሎው ግን ዝቅተኛ ከሚባለው ማህበረሰብ ጋር ነበር።

በ1962 ዓ.ም. ታህሳስ 19 ምሽት ጥላሁን በ29 ዓመቱ መገደሉን ተከትሎ፣ ተማሪዎች በቁጣ አስክሬኑን ወደ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲው በመውሰድ ከሌሎች የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጋር የሀዘን ስነ ስርዓቱ ተካፋይ ሆነዋል።

በተማሪዎች ታጅቦ በቅድስት ሥላሴ እንዲቀበር የአስክሬን ሽኝት ስርዓቱ ግን በመንግስት ታጣቂዎች ተስተጓጎለ። አስክሬኑም ከተማሪዎች ተነጥቆ ተወሰደ። በመንጠቅ ሂደቱ በተኩስ ተማሪዎች ተገድለዋል።

ከሶስት ቀን በኋላ ግን በማይጨው በወዳጅ ዘመዶቹ እና ጥቂት ተማሪዎች አጀባ ቀብሩ ተፈጽሟል። የጥላሁን ግድያ በሁለተኛ ደረጃ እና በዩኒቨርሲቲ የነበረውን ቁጣ አባብሶ ተቃውሞውን እንደገና አፋፍሞታል።

በአብርሃም በለጠ
2022-12-28