ሀገሬ ቲቪ

ጊኒ ከኢቦላ ቫይረስ ነፃ መኾኗ የታወጀበት ዕለት

ዓለማችን ላይ የተለያዩ ወረርሽኞች ተከስተው የበርካታ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፈዋል።

የኢቦላ ቫይረስ ደግሞ ከእነዚህ በፍጥነት ከሚሰራጩ ቫይረሶች አንዱ ነው። ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1968 ዓ.ም በሱዳን ናዛር ዉስጥና ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ያምቡኩ በተባሉ ግዛቶች ነበር።

በዚሁ ግዛት ኢቦላ የተባለው ወንዝ አካባቢ በመታየቱ ነው ቫይረሱ በወንዙ ስያሜ ሊጠራ የቻለው። ከ2007 እስከ 2009 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ደግሞ ይኸው ቫይረስ በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ላይ በሰፊው የተሰራጨበት ወቅት ነበር።

ከእነዚህ ሀገራት አንዷ በኾነችው እና በርካታ ዜጎቿን የተነጠቀችው ጊኒ ነበረች። ሀገሪቱ ታዲያ ከቫይረሱ ነፃ መኾኗ በዓለም ጤና ድርጅት የታወጀው ከ 7 ዓመት በፊት በዛሬዋ ዕለት ነበር።

ሀገሪቱ ከዚህ ቫይረስ ነፃ መኾኗ የታወጀው ከ 42 ቀናት በኋላ የመጨረሻው ታካሚ ሁለተኛ ዙር ምርመራ ተደርጎለት ከቫይረሱ ነጻ መኾኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነበር።

ለኹለት ዓመታት ጊኒን ሲያስጨንቅ የነበረው ቫይረስ በወቅቱ ከ 2ሺ 500 በላይ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ደግሞ ከሞት ጫፍ ደርሰው ማገገም ችለዋል።

ከጊኒ በተጨማሪ ላይቤሪያ እና ሴራሊዮን በወቅቱ የኢቦላ ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ጥሩ ሥራ በመስራታቸው አድናቆትን ተችራቸው ነበር። ይሁን እንጂ ቫይረሱ ጊዜ ጠብቆ እንደገና መመለሱ አልቀረም።

ከዓመት በፊት በየካቲት ወር ይኸው ቫይረስ በጊኒ ተከስቶ ሶሥት ሰዎች መሞታቸው ተነግሮ ነበር። በወቅቱ አንድ የሕክምና ባለሙያ የኾነች ሴት በቫይረሱ ተይዛ ከሞተች በኋላ በቀብር ሥርዓቱ ላይ የተገኙ አራት ሰዎች መያዛቸው ተነግሮ ነበር። በወቅቱ አስቸኳይ አዋጅ በማወጅ ቫይረሱን ለመቆጣጠር ጥረት አድርጋ ነበር።

በዚሁ ዐመት በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ላይ ዳግም የተከሰተውን እና ለብዙ ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነውን የኢቦላ ቫይረስ ለመቆጣጠር የክትባት ዘመቻ ጀምራ ነበር። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ወቅቱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዛመተበት በመኾኑ ለጊኒ ድርብ ፈተና ኾኖባት ነበር። የሟቾች ቁጥርም 11 ደርሶ ነበር።

ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር አፋጣኝ ምላሽ በመሰጠት ቫይረሱ ብዙ ጉዳት ሳያስከትል ዳግም ልትቆጣጠረው ችላለች።

በሙሉጌታ በላይ
2022-12-29