ሀገሬ ቲቪ

አሜሪካ ከኩባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ያቋረጠችበት ዕለት

አሜሪካ እና ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነታቸውን ካቋረጡ ዓመታት ተቆጥረዋል። በ1953 ዓ.ም. ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን በይፋ ያቋረጡት።

ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እና ኩባ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ አለመስማማት ጣሪያ ደርሶ ነበር።

ከዛሬ 62 ዓመታት በፊት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዲዋይት አይዘንሀወር በኩባ ሃቫና የነበረውን የአሜሪካ ኢምባሲ በመዝጋት በይፋ ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ማቋረጣቸውን ገለጹ።

በጊዜው የኩባው ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮ አገዛዝ ለአሜሪካ አልተስማማትም ነበርና ። የካስትሮን አገዛዝ አሜሪካ በመቃወሙ ረገድ ከጫፍ የመድረሷ ማሳያም ነበር።

በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ያውም ከአሜሪካ አፍንጫ ስር ሆና ኮሚዩኒዝምን ማቀንቀኗ ለካፒታሊዝም ዋነኛ አቀንቃኟ ለዩናይትድ ስቴትስ የምትቀበለው አልሆነም። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውም መሻከሩ አልቀረም።

ኩባ የአሜሪካ ኢምባሲ ሰራተኞች ቁጥር እንዲቀንስ መወሰኗ ደግሞ በፍጥነት ወዳጅነታቸው እንዲቋረጥ ለአሜሪካ ምክንያት ሆኗታል። የካስትሮ ኩባ የሰራተኞቹ ቁጥር ይቀነስ ስትል እንደምክንያት ያነሳችው አሜሪካ ኢምባሲዋን ለሰላዮቿ መሸሸጊያነት እየተጠቀመች ነው የሚል ነበር።

በርግጥም የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ፊደል ካስትሮ በ1950ዎቹ መጀመሪያ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ መሻከር ጀምሯል። የካስትሮ አስተዳደር ጠንካራ ጸረ አሜሪካ አቋም አለው የሚል ዕሳቤን የአሜሪካ ባለስልጣናት ፈጥነው መያዝ ጀምረው ነበር። ኩባ ወደ ኮሚዩኒዝም ታመራለች የሚል ፍርሃትም አድሮባቸዋል።

የካስትሮ አስተዳደርም ከሶቭየት ህብረት ጋር ከተመረጠ ብዙም ሳይቆይ ከሶቭየት ህብረት ጋር የንግድ ስምምነትን ተፈራረመ።

የግዜው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የአይዘንሀወር አስተዳደርም ካስትሮን ከስልጣን የሚያስወግድ ቡድንን ወደ ማሰልጠኑ ብሎ በገንዘብም ወደመደገፉ አዘንብሏል።

ካስትሮ በምላሹ የውጭ ዜጎችን እና ኩባኛዎችን ሀብት ብሄራዊ የማድረግ ምላሽን በመስጠት ላይ ነበሩ። አሜሪካ ለዚህም በምላሹ የንግድ እንቅስቃሴዋን ከኩባ ጋር አቋረጠች።

ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ትልቁ መቋጫቸውን ያበሰሩት ግን አይዘንሀወር በዛሬዋ ዕለት በ1953 ዓ.ም. ነበር። በዚህ ዕለት በይፋ ከኩባ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በይፋ ማቋረጣቸው አሜሪካን ከካስትሮ አስተዳደር ጋር ያላትን ወዳጅነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ክየመፍታት ተስፋን ያጨለመ ሁነት ነበር።

ከዚያ በኋላም በሀገራቱ መካከል ያለው ወዳጅነት ብዙም ሳይሻሻል ግማሽ ክፍለ ዘምንን ተሻግሯል።

በአብርሃም በለጠ
2023-01-03