ሀገሬ ቲቪ

ሊግ ኦፍ ኔሽንስ የተመሰረተባት ዕለት

የዓለም አቀፉ ተቋም የሊግ ኦፍ ኔሽንስ መቋቋም ጉልበታም ሀገር ደካማውን እንዳያጠቃ በህብረት ለመቆጣጠር በሚል አላማ ነበር።

ምንም እንኳን ይህንን ግቡን ባለመወጣቱ ቢተችም፣ ይሄው ተቋም በይፋ የተመሰረተው በዛሬዋ ዕለት ከ97 ዓመታት በፊት ነበር። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በሳራጃቮ የኦስትሮ ሀንጋሪው ልዑል ፖለቲካዊ ግድያ ትልቁን እና ደም አፋሳሹን የአንደኛው የዓለም ጦርነትን አስከትሏል።

ለዚህ ጦርነት ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እና እንግሊዝ ብዙ ወጣቶች ሲማገዱ፣ በሀገራቱ ዓለም ከጦርነቱ በኋላስ የሚለው የሰላም ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም።

ከዚሁ የአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዓለም ሰላምን ስለሚያስከብር ዓለም አቀፋዊ ተቋም መቋቋም ተጽዕኖ ፈጣሪ ድምጾች ይስተጋቡም ነበር።

የዚሁ የዓለምን ሰላም የሚያስጠብቅ ዓለም አቀፋዊ ተቋም የማቋቋም ሃሳብን የጊዜው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዉድሮው ዊልሰንም አቀንቃኝ ሆኑ።

በጦርነቱ ማብቂያም ፕሬዝዳንቱ ስለጦርነቱ የመቋጫ መንገዶች ካስቀመጧቸው 14 ነጥቦች አንዱ ዓለም አቀፉ ተቋምን ማቋቋም ይገኝበትም ነበር።

በዚያው የጦርነቱ ማብቂያ ዓመት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጎራዎች መካከል ማዕከላዊ ኃይሎች (ሴንትራል ፓወርስ) መገዳደሉ ይብቃን ሲሉ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ።

እነዚሁ ኃይሎች ከተሸናፊዎቹ ጀርመን እና ኦስትርያ ሀንጋሪን በቨርሳይለስ የመቅጣት ስምምነትን አደረጉ። አሜሪካ በፕሬዝዳንቷ ዊልሰን በኩል የመጨረሻ የሰላም ፍላጎትን ብታሳይም እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ግን ሳይስማሙ ቀሩ።

የቀድሞ ጠላቶቻችን ያሏቸው ሀገራትን የማጥቃት ከፈተኛ ወታደራዊ ዝግጅትን ማድረግን ተያያዙት። በሂደት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ግን ሊግ ኦፍ ኔሽንስን የመስረት ሃሳቡ በኃያላኑ ዕውቅና አግኝቷል።

ዊልሰንም ይሄንንው ተቋምን የማቋቋም ሃሳብን ለአሜሪካ ሴኔት አቅርበዋል። የአሜሪካ ኮንግረስ ግን የአሜሪካን ስልጣን ይገድባል ሲል የሊግ ኦፍ ኔሽንስን መመስረት ተቃውሞታል።

ሊግ ኦፍ ኔሽንስም በተቋሙ መመስረት ገና ያላመነችውን አሜሪካን ትቶ የመጀመሪያ ጉባኤውን በ1911 ዓ.ም. በጄኔቫ አድርጓል።

ቀደም ብለው 42 ሀገራት የመመስረት ነገሩን ካጸደቁ በኋላ በዛሬዋ ዕለት በ1912 ዓ.ም በይፋ ተመስርቷል። ዓለም አቀፍ ሰላምን ለማስፈን የተቋቋመው ተቋሙ የትንንሽ ግጭቶች አደራዳሪ ሆኖ ቢቆይም፣ ለትልልቅ ጉዳዮች ግን በኃያላኑ ፊት ተሰሚነት ያለው ተቋም ለመሆን እስከ 1920ዎቹ ብዙም አልተቻለውም ነበር።

በሩቅ ምስራቅ ኤስያ ጃፓን ቻይናን ስትወር ድርጊቷን አውግዞ የነበረ ቢሆንም ጃፖን ግን ተቋሙን ጸጥ አሰኝታው ነበር። የጀርመንን የእንደገና በከፍተኛ ሁኔታ የጦር መሳሪያ መታጠቅንም ሆነ የጣሊያንን የኢትዮጵያን ወረራን ማስቆም አልተቻለውምም።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መከሰት ደግሞ ተቋሙ የተቋቋመለትን አለም አቀፋዊ ሰላም ማምጣት ያለመቻሉ ማሳያም ሆኗል። ይሄው ተቋም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ዩናይትድ ኔሽንስ) በ1937 ዓ.ም. ተተክቷል።

በአብርሃም በለጠ
2023-01-10