ሀገሬ ቲቪ

በሩሲያ እና አውሮፓውያን በአፍሪካ ጉዳይ

ወትሮም በዩክሬን ጦርነት ጥርስ የተናከሱት ምዕራባውያን እና ሩሲያ ፍጥጫቸውን ወደ አፍሪካ ምድር ማዞራቸው ተሰምቷል።

ማጠንጠኛቸው ደግሞ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ናቸው። በሳሂል ቀጠና የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ዋግነር ለአሸባሪዎች ጡንቻ ሆኗል ፈረንሳይን ጨምሮ የአውሮፓውያኑ የክስ ማጠንጠኛ ነው።

በዚያ በሳሂል በረሀ ሰላም ከራቀ ሰንበት በት ብሏል፤ በመፈንቅለ መንግስቶች ታጅበው ዛሬም ድረስ አሉ። ይህ የሳሂል ቀጠና ያኔ በዚያን ዘመን ፈረንሳይ እንደልብ ትፈነጭበት የነበረ ቀን ግዛቷ ነበር።

ከቀኝ ግዛት ዘመን በኋላ በቀተናው እየጠነከረ የመጣውን የአክራሪ እስላማዊ ሽብርተኞችን እዋጋላው ስትል ወታደሮቿን ውሎ እን አድራቸውን በዚያ አድርጋ ነበር።

ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ነበር የሆነው፤ የአሸባሪዎቹ ጉልበት ከመኮሰስ ይልቅ እየፈረጠመ መጣ። ፈረንሳይም አጋር ያሸኛል በማለት የአውሮፓ ህብረት የጋራ ጦርን በሰው ሀገር ላይ አሰለፈች፤ ነገሩም እየባሰ የአሸባሪዎቹ ጉልበትም እየጠነከረ መጣ።

በዚህ ሁሉ መሀል አለፈ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቶች በቀጠናው ተደረጉ፤ ጊኒ ቢሳው፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጊኒ ኒጀር እና ማሊ።

በኒጀር እና በጊኒ ቢሳው የነበሩት ብቻ ሳይሳኩ ቀሩ፤ የተቀሩት ግን በጉልበት መንግስታቸውን ቀየሩ። ያኔ በቀጠናው የፈላጭ ቆራጭነት ድርሻ የነበራት ፈረንሳይ እና አውሮፓውያኑ አብዝተው ተጨነቁ።

በማሊ የፈረንሳይ ወታደሮች ካምፕ አቅራቢያ የጅምላ መቃብር ተገኘ፤ የአሮፓውያኑ ጣቶች ሁሉ የካምፑ ባለቤትን ትተው የማሊ ወታደሮች ላይ ጠቆሙ።

በማሊ ስልጣኑን የጨበተው ወታደራዊ መንግስት የፈረንሳይ ወታደሮችን ከሀገሩ አባረረ በሀገሪቱ የነበሩ ካምፖቿን የሀገሩ አደረጋቸው በምትኩ አሸባሪዎችን ይዋጋለት ዘንድ ከአውሮፓ ውጪ አጋር ፈለገ ያኔ የዋኘር ግሩፕ የማሊን ወታደሮች ለማገዝ በዚያ ተገኘ።

ያኔ የምዕራባውያኑ ጣቶች በሩሲያ እና ወታደራዊ የማሊ መንግስት ላይ ተነሱ። ትላንትም የሆነው ይህ ነው፤ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና አውሮፓውያኑ ጣታቸውን በሩሲያ ላይ ለመጠቆም ከልካል አልነበራቸውም። ማስረጃ ባላቀረቡበት ክስ ሩሲያን ተጠያቂ አድርገዋታል።

እኛ የማንክደው ወንጀለኛው የዋኘር ግሩፕ በአፍሪካ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባ መሆኑ ነው። ሀብቶችን እየዘረፈ፣ ነብስ እያጠፋ እና የሰላም አስከባሪዎችን ደህንነት አደጋላይ እየጣለ ነው። የቡድኑ በዚያ መገኘት የአሸባሪዎችን እንቅስቃሴ ከመቀነስ ይልቅ ጨምሮታል።

በቀጠናው የዋኘር ግሩፕ እንቅስቃሴ በትክክልም አሸባሪነትን ለመዋጋት አቅም የሌለው መሆኑን ያሳየ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑ በቀጠናው ለተፈፀሙ የሰብዓሚመብት ጥሰቶች በቀጥታ ተጠያቂ ነው።

የዚህ ሁሉ ወቀሳ ማጠንጠኛ የሆነችው ሩሲያ ዝምታን አልመረጠችም። ክሳችሁ ሁሉ የለመዳችሁት የፈጠራ የበሬ ወለደ ትርክቶች ናቸው ብላለች።

ክሱን ያቀረቡ ሀገራት በመላው አሸባሪዎችን በመደገፍ እና ሀገራትን በማመስ የሚሳተፉ እና የሚያደርጉ ናቸው፤ በተለይ በአፍሪካ ሀብቶችን የመዝረፍ ፍላጎት ስላላቸው ሊቢያን አፈራርሰው እና በትነው ሩሲያን ተጠያቂ ለማድረግ ይሞክራሉ። አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል ማመን አይፈልጉም፤ መሪዎቿ ከማን ጋር መተባበር እንዳለባቸው የመምረጥ ነፃነታቸውን መካድ ይፈልጋሉ።

በኢኮዋስ የሚመራውን የሰላም ጥረት እንደግፋለንም ብላለች ሩሲያ። በአፍሪካ ምድር፤ የምድር በረከት በበዛለት ቀጠና ፊት ለፊት የተፋጠጡት መዕራባውያን እና ሩሲያ ነገራቸው ወዴት እያመራ ይሆን ግዜ ሁሉንም ነገር ያሳየናል።

ለዘገባው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዌብሳይት፣ አር ቲን እና አልጄዚራን ተጠቀምን።

በሳምሶን ገድሉ
2023-01-12