መልዕክቶችን ቤት ለቤት ለማድረስ የብሄራዊ የአድራሻ ስርዓት አለመኖሩ እየፈተነው መሆኑን የኢትዮጵያ ፖስታ አስታወቀ። ይህ ቢሆንም አሁንም መደበኛ አድራሻ ላላቸው ነዋሪዎች አገልግሎት ለመስጠት እየተዘጋጀሁ ነው ብሏል።
በዓለማችን ላይ በየቀኑ ከ5 ሚሊዮን በላይ የፖስታ ልውውጦች እንደሚደረጉ የዓለም የፖስታ ህብረት መረጃ ያመለክታል።
ዘርፉ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም እራሱን እያሳደገ የመጣ ዘርፍ መሆኑን ይኸው ሪፖርት ይጠቁማል።
የፖስታ አገልግሎቶች መልዕክቶችን ከላኪው ወደ ተደራሲው ማድረስ መሆኑ በሁሉም ዘንድ ይታወቃል።
ሰዎች ባሉበት የተላከላቸውን መልዕክት እንዲደርሳቸው ለማድረግ ሀገር አቀፍ የሆነ የአድራሻ ስርዓት አለመኖሩ የፖስታ አገልግሎት ፈተና እንደሆነ የኢትዮጵያ ፖስታ ዋን አስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሀና ዓርአያሥላሴ ነግረውናል።
ከሌላው ዓለም አንፃር ሲታይ መሰረታዊ የመንግስት አገልግሎቶች በፖስታቤት በኩል የመስጠቱ ልምድ አናሳ መሆኑ በሀገሪቱ የፖስታ አገልግሎች ላይ ተፅዕኖ እንዳለው የጠቆሙን ኃላፊዋ ተቋሙ እንደ ኢሚግሬሽን ካሉ ተቋማት ጋር በመሆን የፓስፖርት ማድረስ አገልግሎትን በተሻለ መንገድ እየሰተ መሆኑን ጠቁመውናል።
እስካሁን በዓመት ወደ 400 ሺሕ የሚጠጉ ፓስፖርቶችን እያደረሰ ያለው ተቋሙ ይህንን አገልግሎት በብሔራዊ መታወቂያ ላይ ለመስጠት በመነጋገር እንደሚገኝ ሰምተናል።
የቤት ለቤት አገልግሎቶችን ለማስፋት ግን ተቋሙ በቀታይ ለመስራት ያቀደው ምን ይሆን ወ/ሮ ሀና እንዲህ ይመልሳሉ።
በመላው ሀገሪቱ 700 ቅርንጫፎችን ከፍቶ አገልግሎቱን እየሰጠ ያለው የኢትዮጵያ ፖስታ በቀታይ የመንግስት አገልግሎቶችን በአንድ መስኮት ለመስጠት መዘጋጀቱን ወ/ሮ ሀና ነግረውናል።
በሳምሶን ገድሉ
2023-01-13
