
በኮንጎ ያለው "ኤም-23" የተሠኘው አማጺ ቡድን በማዕድን ከበለጸገው ቁልፍ ይዞታው ከነበረው ሰሜን ኪቩ ግዛት ለመውጣት ወስኛለሁ ብሏል።
ከሀገሪቱ መንግሥት ጋር ከወራት በፊት በተደረገው ስምምነት መሠረት ከውሳኔው መድረሱ ተገልጿል።
የቡድኑ አመራሮች በሀገሪቱ የሰላም ስምምነት እንዲደረግ ሲጥሩ ከነበሩት የቀድሞ የኬኒያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ጋር ውይይት አድርገዋል።
"ኤም-23" የተሰኘው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቅ ክፍል ኬቩ በተባለው አካባቢ የሚንቀሳቀሰው አማጺ ቡድን በ2004 ዓ.ም ነበር የተመሠረተው።
ይህ አማጺ ቡድን በኮንጎ በማዕድን ሀብታቸው የበለጸጉ ቦታዎችን በመቆጣጠር እና ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ተደጋጋሚ ጦርነት በማድረግ እስካዛሬ ድረስ ቀጥሏል።
ቡድኑ በሚያደርሰው ጥቃት በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለሞት እና መፈናቀል ተዳርገዋል። ከወራት በፊት ግን ተስፋ የተጣለበትን የሰላም ስምምነት ከዲሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት ጋር አድርጎ ነበር።
የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ፣ የተቆጣጠራቸውን አካባቢዎች እንዲለቅ፣ ትጥቅ እንዲፈታ፣ ታጣቂዎቹ ከሀገሪቱ መከላከያ ኃይል ጋር እንዲዋሃዱ አሊያም እንዲበተኑ የሚሉ አንኳር የሥምምነት ነጥቦችን አማጺ ቡድኑ’’ በጄ’’ ሲል ተቀብሏቸዋል።
አሁን ላይ ታዲያ ከስምምነቱ አንዱ የኾነውን ግዴታ መወጣቱን አስታውቋል። በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ኪቩ ከተባለችው በማዕድን ከበለጸገችው ግዛት ለመውጣት ወስኛለሁ ብሏል።
የቡድኑ አመራሮችም ከቀድሞ የኬኒያ ፕሬዝዳንት እና ቡድኑን እና የኮንጎን መንግሥት የማሸማገል ኃላፊነት ከነበራቸው ከኡሁሩ ኬኒያታ ጋር በሞምባሳ ውይይት ማድረጋቸውን ዘ ኢስት አፍሪካ ዘግቧል።
የኤም23 ሊቀመንበር በርትራንድ ቢሲምዋ ደግሞ ውይይቱን መርተውታል። አማጺ ቡድኑ በሰሜን ኪቩ ኤም23 ኪቡምባ ከተባለች ዋንኛ የገበያ ማዕከል ከኾነች ከተማና ከሩማንጋቦ ካምፕ ቀደም ሲል መውጣት መጀመሩ ነው በውይይቱ የተገለጸው።
ይህንንም የቡድኑ የጦር አመራሮች ተናግረዋል። የቡድኑ ተዋጊዎች የሚለቋቸውን ግዛቶች የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ጦር ይረከባቸዋል ተብሏል።
ይህም ታዲያ በአማጺ ቡድኑ ሲንገላቱ ለነበሩ ሕዝቦች ትልቅ ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጓል። ቡድኑን የሩዋንዳ መንግሥት በአግባቡ እየረዳው ነው ስትል ኮንጎ ተደጋጋሚ ክስ ስታቀርብ ቆይታለች።
ሩዋንዳ በበኩሉ በሀሰት ከተከሰስኩ በቡድኑ ተፈናቅለው ወደ እኔ የሚመጡ ስደተኞችን መቀበሌን አቁሚያለሁ ስትል ካሳምንት በፊት አስታውቃለች።
በሙሉጌታ በላይ
2023-01-13