የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ለሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ሌሎች አስር አባሎችን ደግሞ ከፓርቲው አግዷል። ውሳኔው የተላለፈባቸው አባላት ከድርጅት ህገ-ደንብ እና አሰራር ውጭ በመሆን አፍራሽ ድርጊቶችንና የዲሲፕሊን ጥሰቶችን በመፈጸማቸው ነው ብሏል ፓርቲው። የንቅናቄው ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ንቅናቄው ሥራ አስፈፃሚነታቸውም ሆነ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው በጋራ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ተገዥ ባለመሆን እና ንቅናቄውን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ጋር ሕብረት በመፍጠርና ፣ ንቅናቄው የሃሳብና የተግባር አንድነት እንዳይኖረው በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ስተለገኙ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው መወሰኑን ፓርቲው ገልጿል፡፡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን ለመወሰን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሥልጣን የሌለው መሆኑን ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች መግለጽ እፈልጋለሁ ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል።
በሀገሬ ቲቪ
2022-05-09
