ሀገሬ ቲቪ

በሥጋት የታጀበው የዚምባቡዌ የምርጫ ዝግጅት

ዚምባቡዌ በዚህ ዓመት በሐምሌ አልያም በነሐሴ ወር ሀገራዊ ምርጫዋን ለማድረግ ደፋ ቀና እያለች ነው።

ይሁን እንጂ እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ምርጫ ሁሉ የዚምባቡዌ ምርጫም ገና በዝግጅት ጅማሮ ከዚም ከዚያም የተቃውሞ እና የሥጋት ድምጾች እየተወረወሩበት ይገኛል።

በሀገሪቱ ካሉ ተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ዕውቅ እና የዜጎች ጥምረት ለለውጥ ፕሬዝዳንት የኾኑት ኒልሰን ቺሚሳ በምርጫው ጉዳይ በሰጡት መግለጫ

“ሀገሪቱን እየመሩ የሚገኙት የፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ አስተዳደር በዚህ ዓመት መገባደጃ ላይ በሚካሔደው ምርጫ ላይ ድል ለመቀዳጀት አመጽ እና ብጥብጥ የመብት ጥሰትን ሊፈጥር ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

እርግጥ በዓለም ዙሪያ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም በኛም ሀገር ሊፈጠር የሚችለው ቀውስ እና ችግር የከፋ ሊኾን ስለሚችል ዓለም አቀፍ ማኀበረሰብ ትኩረቱን ያድርግ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል ተፎካካሪው ኒልሰን ቺሚሳ።

የሀገሪቱ ዜጎች ለውጥን እና ዕድገትን እንደሻቱ ነው። ነገር ግን ሰዎች በሚያራምዱት ግላዊ የፖለቲካ ሐሳብ እየተገደሉ ነው ብለዋል።

ዚምባቡዌን ለ37 ዓመታት የመሩት ሮበርት ሙጋቤ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ይህ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ የሚደረግ ይኾናል። ሙጋቤን በ2009 ዓ.ም ተክተው ወደ ስልጣን የመጡት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እስካሁን ድረስ ሀገሪቱን እየመሩ ይገኛል።

ከሙጋቤ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ በኋላ የመጣው አስተዳደር የዴሞክራሲና የተጠያቂነት ተስፋን ያዘለ የነበረ ቢኾንም ዕውነታው ግን ተቃራኒው ኾኗል ሲሉ በርካታ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ያነሳሉ።

የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት መጎዳት በተለይም ከ አራት ዓመት በፊት የነዳጅ ዋጋ ከፍ ማለት እና በዚህም የተነሳው ሕዝባዊ አመጽ በጸጥታ ኃይሎች እርምጃ 12 ሰዎች ሲሞቱ ከ70 በላይ መጎዳታቸው ይታወሣል።

ይህም በስልጣን ላይ ያለው አመራር ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ጨካኝ እና ተንኮለኛ ናቸውም ይባላል። በዚህ ባሕሪያቸው ኮሮኮዳይ ወይም አዞ የሚል ቅጽል ስም እንደተሰጣቸው ነው ዘጋርዲያን የጻፈው።

በዚህ ዓመት የሚደረገው ምርጫ ታዲያ በብዙ ወጀቦች የታጀበ ይኾናል ተብሎ ተጠብቋል የዚምባቡዌ የዋጋ ግሽበት በየዓመቱ ከ250% እስከ 400% እንደሚደርስ ይገመታል።

የዓለም ባንክ ምጣኔ ሀብቱ በተያዘው በጀት ዓመት ይበልጥ እንደሚቀንስ ተንብይዋል።

በሙሉጌታ በላይ
2023-01-23