ሀገሬ ቲቪ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሜይልአሜሪካስ ስምምነት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አዲስ አበባን ማዕከል አድርጎ በመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ተወዳዳሪ የኢኮመርስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስምምነትን ከሜይልአሜሪካስ ጋር አደረገ።

አየር መንገዱ ከሜይልአሜሪካስ ጋር ከ20 በላይ ሀገራት የጋራ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኢኮመርስ አገልግሎት ከሚሰጠው ሜይልአሜሪካስ ጋር ስምምነት አድርጓል። አየር መንገዱ በ40 ሀገራት የኢኮመርስ አገልግሎት ከሚሰጠው የሜይልአሜሪካስ የግል የፖስታ ኦፐሬተር ጋር ነው ስምምነቱን ያደረገው።

በአፍሪካ በማጓጓዝ የካርጎ አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚ የሆነው እና በብዙ ዘርፎች ውጤታማ እየሆነ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የዓለም አቀፉ የፖስታ ማህበር አባል የሆነው ሜይልአሜሪካስ አዲስ አበባን ማዕከል አድርጎ በአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ተወዳዳሪ የሆነ የኢኮመርስ አገልግሎት ለመስጠት መስማማታቸው ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ከሜይልአሜሪካስ ጋር በመቀናጀታችን ደስተኛ ነን ያሉ ሲሆን እስካሁን ከዚሁ የኢኮመርስ አገልግሎት ሰጭ ተቋም ጋር እስካሁን በአፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ ከ20 በላይ በሚሆኑ ሀገራት አገግሎት እየሰጠን ነው ብለዋል።

ስምምነቱ እየሰጠን ያለነውን አገልግሎት አሻሽሎ ለማስፋት እና ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን እንደሚያግዝም ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

የሜይልአሜሪካስ ፕሬዝዳንት ቶማስ ሚገንስ በላቲን አሜሪካ ቀዳሚ ድንበር ዘለል የኢኮመርስ አገልግሎት ሰጭ ተቋምነታችን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር በአፍሪካ ተደራሽነታችን ለማስፋት በመስማማታችን ተደስተናል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከ25 ዓመታት በላይ በዘርፉ ላይ ልምድ ያለን ሲሆን በአፍሪካ ከቀዳሚው የአየር መንገድ ጋር መስማማታችን ለደንበኞቻችን ንብረቶቻቸውን የምናቀርብበትን ፍጥነት ለማሻሻል ያስችለናል ብለዋል።

አየር መንገዱ ለዕቃ ማጓጓዝ የካርጎ አገልግሎት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን በአመት 150 ሺህ ቶን ማስተናገድ የሚችል የኢኮመርስ ማዕከልን በአዲስ አበባ እያሰገነባ መሆኑም ተጠቁሟል።

ይሄው ማዕከልም ዘመናዊነቱን የጠበቀ ሆኖ እንዲሰራ የታሰበ ሲሆን ይሄኛው ስምምነት ደግሞ የካርጎ አገልግሎቱን ለማስፋት ለአየር መንገዱ አጋዥ እንደሚሆነው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለካርጎ ወይም የማጓጓዝ አገልግሎት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን በዘርፉ ከአፍሪካ ቀዳሚነቱንም እንዳስጠበቀ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሜይልአሜሪካስ ይሄንንው ወዳጅነታቸውን እያጠነከሩ እንደሚሄዱ ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ለሜይልአሜሪካስ የማጓጓዝ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በላቲን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አፍሪካ እና ሌላውም የዓለም ክፍል የሜይልአሜሪካስን ትስስሮች በመጠቀም ተወዳዳሪነቱን የማጎልበት ዕድልን ስምምነቱ ይሰጠዋል ተብሏል።

በአብርሃም በለጠ
2023-01-23