
ኬኒያ በአንድ አመት ውስጥ በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ዜጎቿ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ አግኝታለች፡፡ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቿ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጮቿ መሆናችው ተዘግቧል፡፡
ሀገራት የውጭ ምንዛሪን ከሚያካብቱባቸው መንገዶች ቀዳሚው የወጪ ንግድ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሀገራት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቿቸው ወደ ሀገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጫቸው ስለመሆኑ ይነገራል፡፡
ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ ሀገራትም ከፍተኛ የሚባለውን የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙት በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ዜጎቻቸው ከሚልኩት ገንዝብ ነው፡፡
እንደ ዓለም ባንክ መረጃ በዚህ ቀጠና የሚኖሩ ሀገራት በጎርጎሮሳውያኑ 2021 ብቻ 49 ቢሊዮን ዶላር ከዚህ ምንጭ አግኝተዋል፡፡ ይህም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ14 በመቶ ጭማሪ የነበረው ሲሆን ከ2018 በኋላም ትልቁ ነው ፡፡
ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኬኒያ ደግሞ በ2022 ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ያገኘችው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቿ ከላኩላት ገንዝብ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
እንደ ሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ መረጃ ኬኒያ በ2022 ከሬሚታንስ ወይም በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዜጎቿ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ አግኝታለች፡፡ ከዘርፉ የተገኘው ገቢ በ8 ነጥብ 34 በመቶ እድገት አሳይቷል ያለው ባንኩ ሬሚታንስ አሁን ላይ ዋነኛ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኗልም ብሏል፡፡
ናይሮቢ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቿን በተመለከተ የምትከተለው ፖሊሲ ትችት የሚቀርብበት ቢሆንም ዘንድሮ ከእነዚህ ዜጎቿ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ የሀገሪቱ ዋነኛ የውጪ ንግድ ከሚባሉት ቡና፣ ሻይና እና የሆርቲካልቸር ምርቶች ሽያጭ ከተገኘው ገቢም የላቀ ሆኗል።
ናይሮቢ ከውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ዜጎቿ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ቁጥር ከፍ ይበል እንጂ በ2022 ለውጭ ገበያ ያቀረበችው ምርት ያስገኘላት ገቢም የ7 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አስመዝግቧል፡፡
የፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አስተዳደር በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቹን በተመለከተ ጠንካራ ስራ ለመስራት መዘጋጀቱን የገለፀ ሲሆን በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኬኒያውያን ለሚገጥማቸው ማናቸውም ጉዳይ መፍተሄ የሚሰጥ አካል በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በኩል ማቋቋሙንም አስታውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቹ እንደ ምርጫ ባሉ ፖለቲካዊ ሂደቶች ተሰታፊ እነዲሆኑ እንደሚሰራም የዊሊያ ሩቶ አስተዳዳር አስታውቋል፡፡
ኬኒያ አባል የሆነችበት እና ሌሎች የቀጠናው ሀገራትን ያቀፈው የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ጥምረትም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቹ በአከባቢው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ስለለመሆኑም ነው የገለፀው፡፡
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የምስራቅ አፍሪካ ዲያስፖራዎች የቀጠናው ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ባለፈው ዓመት ብቻ በ35 በመቶ እንዲያድግ ትልቅ ሚና ነበራቸው ተብሏል፡፡
በቀጣው በ2022 8 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንስትመንት ፈሰስ ተደርጓል ሲል የዘገበው ዘኢስት አፍሪካን ነው፡፡
በወንድምአገኝ አበበ
2023-01-24