ሀገሬ ቲቪ

ተላላፊ ላልሆኑ ሕመሞች ዝቅተኛ ትኩረት መኖሩ ተገልጸ

በሀገራችን የጤና ዘርፉ የበጀት (ፋይናንሲንግ) ስርዓት ተላላፊ ላልሆኑ ሕመሞች ያለው ትኩረት ደካማ መሆን የሕመሞቹን ጉዳት ለመቀነስ ተግዳሮት መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ማህበራት ህብረት በሕመሞቹ የሀገራችን ትኩረት ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

በጤና ሚኒስቴር የጤና መድኅን አገልግሎት ዘርፍ ም/ዋ/ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉቀን አርጋው የጤናው ዘርፍ መንግስት፣ አጋር አካላት እና የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ክፍያ የፋይናንስ ምንጮቹ ሲሆኑ የአጋር አካላት ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል።

የኤንሲዲአይ ፖቨርቲ የምስራቅ አፍሪካ አማካሪ ዶ/ር ዉባይ ዋለልኝ ባለፉት ዓመታት ትኩረታችንን ተላላፊ ከሆኑ ሕመሞች፣ የእናቶች እና ህጻናት ጤና ላይ እና ስርዓተ ምግብ ላይ ስናደርግ ለተላላፊ ላልሆኑ ሕመሞች ዝቅተኛ ትኩረት መኖር የሕመሞቹ ጉዳት እንዲጨምር አድርጎታል ብለዋል።

ዶ/ር ዉባይ የጤና ተቋማቶች ለተላላፊ ላልሆኑት ሕመሞች ያላቸው አገልግሎት፣ የመመርመሪያ መሳሪያዎች እና መድሃኒቶች አቅርቦት ደካማ መሆኑንም ገልጸዋል።

የተላላፊ ሕመሞችን ጉዳት በመቀነሱ ረገድ በህክምና ወጭ ስጋት ወደ ጤና ተቋማት ከመሄድ ወደ ኋላ የሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው እንቅፋት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ዶ/ር ሙሉቀን አርጋው ይሄንን ስጋት በመቀነሱ ረገድ የጤና መድኅን አገልግሎት ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የተላላፊ ሕመሞችን ጉዳት ለመቀነስ ጤናማ አኗኗር እንዲጎለብት ማድረግ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

በአብርሃም በለጠ
2023-01-24