ሀገሬ ቲቪ

በቱርክ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ

በቱርክ እና ሶርያ ድንበር አቅራቢያ የደረሰ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በሰው ህይወት እና የንብረት ውድመት አስከተለ።

አደጋው ቱርክን ጨምሮ ፤ ሶርያ ፤ ሊባኖስ እና ሳይፕረስ ላይ ተከስቶ እስካሁን ከ 1 500 በላይ ሰዎች እንደሞቱ ተገልጿል።

በዓለማችን ከፍተኛ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ይደርስባቸዋል ከሚባሉ ሀገራት ውስጥ ስሟ የሚጠቀሰው ቱርክ በርካታ ዜጎቿን የቀጠፈ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶባታል።

በደቡብ ምስራቅ ቱርክ ከሶሪያ ድንበር አቅራቢያ የተከሰተው ይህ ያልተጠበቀ አደጋ እስካሁን ባለው መረጃ 284 ቱርካዊያንን ገድሎ 2,323 እንደቆሰሉ የቱርክ ምክትል ፕሬዝዳንት ፉአት ኦክታይ ተናግረዋል።

ከ11 ዓመታት በላይ በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ክፉኛ የተጎዳችው ሶሪያም በዚህ አደጋ ከ237 በላይ ዜጎቿን ያጣች ሲሆን ከ600 በላይ ሰወች ከፍተኛ አደጋ ደርሶባቸዋል።

በአደጋው መኖሪያ ቤቶች እና ሕፃዎች ፈራርሰዋል፡፡ በፍርስራሽ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለማዳን በሚደረገው ጥረት አዳዲስ ሟቾች እየተገኙ እንደሆነ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ይህ አደጋ በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ፤ ሶርያ ፤ ሊባኖስ እና ሳይፕረስን ጨምሮ በሌሎች 10 ከተሞች የተከሰተ ሲሆን ከሰው ነፍስ በተጨማሪ ከፍተኛ የንብረት ውድመት አስከትሏል።

በዲያርባኪር ከተማ የሚገኝ ግዙፍ የገበያ መዐከልም ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የቱርክ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ሱሌይሞን ሶይሉ አስታውቀዋል።

እጅግ አሰቃቂ አደጋ ተከስቷል። ሁላችንም ደንግጠናል ። አሁን የመንግስት አካላት ፤ ፖሊሶች እንዲሁም ሁሉም ዜጋ አደጋው በተከሰተበት ቦታ ሰወችን ለማትረፍ እየተረባረቡ ነው። ፍርስራሾች ውስጥ ያሉ ሰወችን ለማዳን የተቻለንን እያደረግን ነው።

የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በጋዚያንቴፕ ከተማ አቅራቢያ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ 17.9 ኪሜ ጥልቀትና በሬክተር ስኬል 7.8 የተለካ አደጋ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

ቱርክ የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ ከሚደርስባቸው ሀገራት አንዷ ስትሆን እ.ኤ.አ. በ 1999 በቱርክ ሰሜን ምዕራብ ክፍል በደረሰ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከ17,000 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው ።

ዛሬ የተከሰተው አደጋም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ሞተዋል።

በዮሴፍ ከበደ
2023-02-06