ሀገሬ ቲቪ

የሰሃራ በታች ሀገራት የሽብርተኝነት ፈተና

ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሀገራት አዲስ የጽንፈኝነት ማዕከል እየሆኑ ነው ተባለ። በ2021 በዓለም ዙሪያ በሽብርተኝነት ምክንያት ከተመዘገበው ሞት ግማሽ ያክሉ በእነዚህ ሀገራት የተፈጸመ ነው ብሏል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለም አቀፋዊ ልማት ኤጀንሲ በሪፖርቱ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የልማት ኤጄንሲ ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት አዲስ የጽንፈኝነት ማዕከል መሆናቸውን ባወጣው የቅርብ ሪፖርት አስታውቋል። በሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ታጣቂ ቡድኖችን የሚቀላቀሉ ሰዎች ቁጥር በ57 በመቶ መቀነሱን ሪፖርቱ ጠቁሟል።

ይሄው ጽንፈኝነትን የተመለከተው ሪፖርት እንዳለው ከጎርጎሮሳውያኑ 2017 ጥናት አንጻር 92 በመቶ የሚሆኑት አዳዲስ የጽንፈኛ ቡድኖቹ ምልምሎች የተሻለ ሕይወት ለማግኘት በሚል ቡድኖቹን የተቀላቀሉ መሆናቸውን ገልጿል።

የተባባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥናት እንደጠቆመው ብዙ አፍሪካውያን ኑሯቸው በኮቪድ 19፣ በከፍተኛ የዋጋ ውድነት እና በአየር ንብረት ቀውስ ሳቢያ በከፍተኛ ሁኔታ እንደተጎዳ ያስባሉም ብሏል።

ለዚህ አዲስ ሪፖርት 2200 ያክል የጽንፈኛ ቡድኖች አባላት ምላሽ የተካተተ ሲሆን ከእነዚህም ግማሽ ያክሉ ፈቅደውም ይሁን ተገደው የቀድሞ የጽንፈኛ ቡድኖቹ አባል እንደነበሩም ተጠቁሟል።

ከተጠያቂዎቹ መካከልም የናይጀሪያው ቦኮሃራም፣ የሶማሊያው አልሻባብ እና ሌሎች ቡድኖች አባላት ተካተውበታል።

በቅርብ አምስት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ከ4 ሺህ በላይ የተመዘገቡ የሽብር ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን 18500 የሚደርስ ሞት ተመዝግቦባቸዋል። ከአህጉሩ ሀገራትም ሶማሊያ ከፍተኛውን ጉዳት ያስተናገደች ሀገር መሆኗ ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ኃላፊ አቺም ስቴይነር ይሰሃራ በታች ሀገራት የጽንፈኛ ቡድኖች አዲስ ማዕከላት እየሆኑ ሲሆን 48 በመቶ የሚሆነው የ በ 2021 በዓለም ዙሪያ በሽብርተኝነት ምክኛት ከተመዘገቡ ሞቶች 48 በመቶ ያክሉ በእነዚህ ሀገራት የተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።

ኃላፊው ስቴይነር በጣም ወጭ የሚያስወጣው ሽብርተኝነትን መዋጋት ብቻ ሳይሆን መፍትሄው የዜጎች ወደ ጽንፈኛ ቡድኖች የሚቀላቀሉበትን መሰረታዊ ምክንያትም መለየት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። የዜጎችን ህይወት ማሻሻልንም ሀገራት ትኩረት ሊሰጡበት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

በአብርሃም በለጠ
2023-02-08