የቀረ ያረጀ ብሎም የተዘነጋው የጎጂ ባህል ጉዳይ ዛሬም ለበርካታ ሴቶች የጤና እክል እና ሞት ምክንያት ነው፡፡
ጉዳዩን በተደጋጋሚ ከመስማት ብዛት ቢያሰለችም ያን ያክል ትኩረት አለመሰጠቱን ግን በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የሚወጣው ዓመታዊ ጥናት አመላካች ነው፡፡
የሴት ልጅ ግርዛት በአብዛኛው የሚካሔደው ከጨቅላነታቸው እስከ ጉርምስና ባለው ጊዜ ውስጥ እና አልፎ አልፎም በአዋቂ ሴቶች ላይ ነው፡፡ በምዕራብ፣ምስራቅ እና ሰሜን-ምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ እና እስያ ሀገራት የሴት ልጅ ግርዛት በሚተገበርባቸው 30 ሀገራት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ጊዜ ከ200 ሚሊዮን በላይ ልጃገረዶች እና ሴቶች ድርጊቱ ተፈጽሟባቿል፡፡
ካሮላኒ ቸርኩት ትባላለች በ14 ዓመቷ ነው የተገረዘችው እድሜዋ ቢሄድም በጣም ችግር ላይ መሆኑን ትናገራለች
"ከተገረዙ በኋላ ወዲያው ፀነስኩ ፤ ልወልድ ስል ህፃኑን መግፋት በጣም አቅቶኝ ነበር፤ ዶክተሮቹ ብረቶችን ተጠቅመው ነው ህጻኑን ያወጡት፤ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሽንቴን መቆጣጠር አልችልም፡፡"
በኡጋንዳም ይህ ባህል አሁንም ድረስ አለ፡፡ኤልሳቤት ቻሚስቶ የተባሉት ግለሰብ ወንጀል እንደሆነ እንኳን ጠንቅቀው አያውቁም ረጅም ዓመታትን በግርዛት ስራ ላይ ተሰማርተዋል እናም ትክክል እንደሆኑ እና ስራቸው እንደሆነ ነው ሚያስቡት፡፡
"ልጃገረዶቹን ስገርዛቸው ርህራሄ የለኝም፤ ገርዤ ከጨረሱ በኋላ ሁሉም ደስ ይላቸዋል፡፡ ሰዎች በደስታ ይዘምራሉ እንዲሁም ይጨፍራሉ፡፡"
በዓመት ከ3 ሚሊዮን በላይ ልጃገረዶች ለግርዛት ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል ታዲያ የሴት ልጅ ግርዛት ዓለም አቀፍ ስጋት ነው ይላል የአለም ጤና ድርጅት መረጃ፡፡
በኬንያ ይህንን ህገወጥ ድርጊት ለመቃወም የተመሰረተው ድርጅት የጥቃቱ ሰላባ የሆኑ ልጃገረዶችን በማስተማር በአከባቢያቸው እንዲቃወሙ ብሎም እንዲያስተምሩ ስልጠና በመስጠት በርካታ የኬንያ ገጠራማ አካባቢዎች ላይ ለውጥ ማምጣት ስለመቻሉ የሲጄቲኤን ዘገባ ያሳያል ፡፡
የድርጅቱ አስተዳዳዳሪ አጌነስ ፕራዮ በርካታ ልጃገረዶችን በመሰብሰብ ድጋፍ ያደርጋሉ ስለጉዳዩም እንዲህ ይናገራሉ፡፡ ብትጮሁም የሚሰማችሁ የለም ይላሉ በምሬት፡፡
"ደምህ ይፈሳል ፤ምንም ዶክተር ወይም ነርስ የለም ፤ በአጠገብህ የሚረዳ ማንም የለም፤ ብትጮህ ወይም ብታለቅስ ማንም አይሰማህም ምክንያቱም አባትህ አጠገብህ አለ፡፡ለእነዚህ ልጃገረዶች እንቢ በሉ እያልኩ እመክራቸዋለሁ የሴት ልጅ ግርዛት ጎጂ ባህል ነው እላቸዋለሁ::
ከጤናው ባለፈ ምጣኔ ሃብትም ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል ባይ ነው የዓለም ጤና ድርጅት፡፡
የሴት ልጅ ግርዛትን የጤና ችግሮች ለማከም የሚወጣው ወጪ ጥናት የተደረገበት ሲሆን መረጃው በተገኘባቸው 27 ሀገራት አሁን ያለው ወጪ በአንድ ዓመት በድምሩ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡
ይህ መጠን በ30 ዓመታት ውስጥ ወደ 2.3 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል የሴት ልጅ ግርዛት ሥርጭት ተመሳሳይ ሆኖ ከቀጠለ የ68 በመቶ ጭማሪ ይኖረዋል ይላል፡፡ በሌላ መልኩ ሀገሮች የሴት ልጅ ግርዛትን የሚያስቆሙ ከሆነ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ውስጥ እነዚህ ወጪዎች በ60 በመቶ ይቀንሳሉ ተብሎ ይገመታል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-05-10
