ሀገሬ ቲቪ

እለቱን ከታሪክ - አሜሪጎ ቬስፑሲ

አሜሪጎ ቬስፑሲ በ15ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ አዲሱ ዓለም በአሁኑ አጠራር ወደ አሜሪካ አህጉር ጉዞ ማድረግ የቻለ አሳሽ ነው። ከአውሮፓ ተነስቶ ወደ ደቡብ አሜሪካ አህጉር ስፔይንን ወክሎ አሰሳ አድርጓል።
ክርስቶፎር ኮሎምበስ አስቀድሞ ወደ አዲሱ ዓለም ጉዞ ማድረግ ቢችልም የቬስፑሲ ስም በአውሮፓ በፍጥነት ናኝቷል። ለአውሮፓ አዲሱ ዓለምም በአሜሪጎ ቬስፑሲ ስም አሜሪካ ተብሎ እንዲጠራ ሆኗል።

የአሰሳ ጉዞውን የጀመረው በዛሬዋ እለት ከ525 አመታት በፊት በፈረንጆቹ 1497 ነበር።የአሜሪካ አህጉር በስሙ የተሰየመለት አሜሪጎ ቬስፑሲ የጣሊያን ውልደት ያለው ነጋዴ እና አሳሽ የነበረ ሰው ነው። ስፔይን የባህር አሳሾችን ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች ስትልክ በመርከብ ዝግጅት ከሚተባበሩ አንዱ ነበር። ቀደም ብሎ ማሰስ ለጀመረው የክርስቶፎር ኮሎምበስ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ጉዞ በመርከብ ዝግጅት ተባባሪ ሆኗል። ኋላም ሴቪላ ለተሰኘው ድርጅት ኃላፊ ሆኗል።

በ15ተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በተደጋጋሚ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ጉዞ አድርጓል። ከእነዚህም ከስፔይን በአሎንሶ ዲ ኦጀዳ አዛዥነት የተከናወነው የአራት መርከቦች ጉዞ በቬስፑሲ መጠናቀቁ ይጠቀሳል። ከዚያ ቀደም ብሎም ሌላ ጉዞ ወደ ሜክሲኮ የባሕር ሰርጥ እና የፍሎሪዳ የአትላንቲክ ጫፍ ጉዞ ማድረጉ ይነገራል። የመጀመሪያ ጉዞውን ማድረግ የጀመረው ግን በዛሬዋ እለት በፈረንጆቹ 1497 ነው።

አሜሪጎ ቬስፑሲ በጣሊያን ፍሎረንስ የተወለደ ሲሆን ኋላም የስፔይንን ዜግነት አግኝቷል። የቬስፑሲ ቤተሰቦች ጣሊያንን ለረዥም ጊዜ ይመሩ የነበሩት የሜዲቺ ቤተሰቦች ጋር ቅርበት ነበራቸው። በ20ዎቹ እድሜው ወደ ንግድ እንዲገባ የተገደደው ቬስፑሲ በተለያዩ ንግዶች ላይ ተሰማርቷል። በፍሎረንስ ሲሰራ ከቆየ በኋላ ኋላም በሴቫይል ስፔይን በባንክ የንግድ ስራ ላይ ተሰማርቷል። ኋላም የአሰሳ ተግባር በስፔይን መንግስት ድጋፍ እንዳለው በመገንዘቡ ሳይዘገይ ወደ አሰሳው ስራ ተጠግቷል። በተደጋጋሚ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ጉዞ ያደረገው ቬስፑሲ በፈረንጆቹ በ1501 ባደረገው በሶስተኛውና ስኬታማው ጉዞው ርዮ ዲ ጀነሬን እና ርዮ ዲ ፕላታን አግኝቷል።

ሶስተኛ ጉዞውን ያደረገው ለፖርቹጋል መንግስት ነበር። ይሄው ጉዞው በጣም የተሳካ ጉዞው ተደርጎ ይቆጠራል። በዚህም አዲስ ዓለም አዲስ አህጉር እንዳገኘ አምኗል። ወደ ፍሎረንስ በላከው ደብዳቤም ደቡብ አሜሪካን አዲስ ዓለም ሲል ጠርቶታል።

አንዳንድ አጥኝዎች የሌሎችን የልፋት ስም ያላግባብ የያዘ ሰው ቢሉትም ከቀደምት የአዲሱ ዓለም አሳሾች አንዱ አቅኝ በመሆን ብሎም የአዲሱ ዓለም የጉዞ ስነ ጽሁፍ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል። የአሜሪጎ ቬስፑሲ የአዲሱ ዓለም የጉዞ ዘገባ በአውሮፓ በፍጥነት ተሰራጨ።

የቬስፑሲን የጉዞ ደብዳቤዎች እንደመመሪያ በመጠቀም የጀርመን ካርቶግራፈር ማርቲን ዋልደስሙለር በፈረንጆቹ በ1507 አዲስ ካርታ ፈጠረ። አሁን ደቡብ አሜሪካ የምንለውን ክፍል ለቬስፑሲ ክብር አሜሪካ “የአሜሪከስ መሬት” ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ ሰየመው። እስካሁንም የአሜሪካ አህጉር ለአሜሪጎ ቬስፑሲ ክብር በተሰየመለት አሜሪካ በሚል ስያሜ ይጠራል።
ጣሊያናዊው ቬስፑሲ የስፔይንን ዜግነት በ1505 ካገኘ ከሶስት ዓመታት በኋላ የዋና አሳሽ ማእረግ በስፔይን ተሰጥቶት አሳሾችን በመልመል እና በማሰልጠን አሳልፏል። ኋላም በወባ በፈረንጆቹ በ1512 በሴቫይል ስፔይን አርፏል።

በአብርሃም በለጠ
2022-05-10