የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ፦
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ብልጽግና አንድ ሆኖ ሁለንተናዊ እድገት ከማምጣት ይልቅ ከመግለጫዎች ጀምሮ ልዩነት ይስተዋላል፣ ችግሩ ምን እንደሆነ ተጠይቋል፡፡
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የዜጎች መፈናቀል አለ፣ በተለይም ዜጎች ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ እየተከለከሉ ነው፤ ሰዎች እየታገቱ፣ የታመሙ ሰዎች በጊዜ ለህክምና ባለ መድረሳቸው በመንገድ ላይ ሞተዋል፣ የእህል ምርት ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ እየገባ አይደለም፣ መፈናቀል አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ምን እርምጃ እየተወሰደ ነው፣ በቀጣይስ ምን ታስቧል? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
የዜጎችን ደኅንነት እና የአገርን ሉዓላዊነት መጠበቅ ዝቅተኛ የመንግስት ኃላፊነት ሆኖ ሳለ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ይገደላሉ፤ ይፈናቀላሉ፤ ቤታቸው ይፈርሳል፤ ንብረታቸውም ይወድማል።
የአገር ሉዓላዊነትን በሚዳፈር መልኩ የጎረቤት አገራት ሰራዊቶች በኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ወሰኖች በርካታ ኪሎሜትሮችን ዘልቀው በመግባት ወረራ ፈጽመዋል፤ አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የዜጎች ደኅንነትና የአገር ሉዓላዊነት ዋነኛ የስጋት ምንጭ ሆኖ የምናየው ራሱ መንግስትን ነው።
የህዳሴው ግድብ ግንባታ ያለበት ሁኔታና ከእርሱ ጋር ተያይዞ የሚደርሱ የፖለቲካ ጫናዎች እንዴት ይታያሉ? የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡
በብሩክታዊት አስራት
2023-03-27
