ሀገሬ ቲቪ

በስርዓተ ምግብ ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በስርዓተ ምግብ ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ትኩረቱን በስርዓተ ምግብ እና በምግብ ውስጥ ባሉ ንጥረ ነገሮች እጥረት ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደዘርፍ ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እየሰራንባቸው ከሚገኙ መስኮች መካከል አንዱ የስርዓተ ምግብ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በተለይም መቀንጨርና መቀጨጭን በመቀነስ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት በመሰራቱ መሻሻሎች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የንጥረ ነገሮች መጓደል ሕፃናት እና ወጣቶች በትምህርት ገበታ፣ በፈጠራ እና ምርምር መስክ ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል ሲሉም ዶክተር ደረጄ አክለዋል፡፡

በተለይ በየዓመቱ በርካታ እናቶች በደም እጥረት ህይወታቸው እንዲያልፍ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል የብረት (የአይረን) እጥረት ዋና ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም በጤናው ዘርፍ ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ በመግለፅ፤ የስርዓተ ምግብ ችግር የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመግታት የፓርላማ አባላቱ ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ነው ዶክተር ደረጄ ያስታወቁት።

የሆፕ-ኤስ.ቢ.ኤች በኢትዮጵያ (HOPE-SBH Ethiopia) ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ቤዛ በሻ በበኩላቸው በሀገራችን 50 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት ከፎሊክ አሲድ እጥረት ጋር እንደሚወለዱ ገልጸዋል።

ይህም ለአካላዊ እና አዕምሮዋዊ እንዲሁም ከባድ ለሆኑ ውስብስብ የጤና እክሎች እንዲጋለጡ መንስኤ ይሆናል ብለዋል፡፡

በቀላሉ ልንከላከላቸው በምንችላቸው የጤናና ተያያዥ ምክንያቶች በርካታ ሕፃናትን፣ ሴቶችን እና ወጣቶችን እያጣንና የሀገርም ኢኮኖሚ እየተጎዳ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ገልፀዋል።

በብሩክታዊት አስራት
2023-03-30