የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩትን የምክር ቤት አባል የዶክተር ጫላ ዋታን ያለመከሰስ መብት አንስቷል።
ዶክተር ጫላ ዋታ በሙስና ወንጀል በመጠርጠራቸው ምክንያት ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ፍትህ ሚኒስቴር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በመጠየቁ የውሳኔ ሀሳብ መቅረቡን የምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱ ገልፀዋል።
የምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከፍትሕ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር ውይይት መደረጉንና ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ጥያቄ የቀረበባቸው የምክር ቤት አባል ጠርቶ ማነጋገሩንም አመልክተዋል።
በዚሁ መሰረት ዶክተር ጫላ የተጠረጠሩበት ወንጀል ለመፈፀማቸው በቂ አመላካች ነገር መገኘቱን አረጋግጧል ብለዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ጉዳዩን በጥልቀት ከተመለከተ በኋላ የምክር ቤቱ አባል የሕግ ከላላ መነሳት ጥያቄን በሙሉ ድምፅ ማፅደቁ ተጠቅሷል።
ምክር ቤቱ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የቀረበውን ሀሳብ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
በማህሌት አማረ
2023-04-04
