
የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት ጦርነት ውስጥ የገቡት የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ አሳሰበ።
የሱዳን ሕዝብ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ወደ ነበረበት እንዲመለስ እና በሲቪል መራሽ መንግሥት ለመተዳደር ያቀረበውን ጥያቄ እና ለዚሁ የሚደረግን ጥረት እንደሚደግፍ ምክር ቤቱ አስታውቋል።
ለሱዳን ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ ፖለቲካዊ አመለካከት ነፃነት እና የሀገሪቱ የግዛት አንድነት መከበር እንዲሁም ቀጣይነት ድጋፉን ዳግም አረጋግጧል።
በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን የገለፀው ምክር ቤቱ፣ ችግሩ ወደ ከፍተኛ ቀውስ ሊሸጋገር እንደሚችልም አሳስቧል።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ሽግግር ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ሊያደናቅፍ ይችላል ሲልም ስጋቱን ገልጿል።
በጦርነቱ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞችን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት ማስከተሉን ጠቅሶ ድርጊቱን በጥብቅ እንደሚያወግዝም አስታውቋል።
በብሩክታዊት አስራት
2023-04-17