ልጅ በረከት ነው። ይህ እሳቤ በበርካታ ዓለማት ላይ የሚታመንበት ነው።
በአንድ ሀገር ውስጥ ደግሞ መኖር ያለበት ህዝብ ካልተመጠነ የልጅ በረከትነቱ ይቀርና መከራ ይሆናል ይላሉ የስነ ህዝብ አጥኚዎች።
ታዲያ በአንድ ሀገር ውስጥ ያለውን የህዝብ ቁጥር ለመመጠን የተለያዩ እርግዝና መከላከያዎችን ዜጎቻቸው እንዲጠቀሙ ይመክራሉ።
በቬንዚዌላ አንድ ሃኪም ነኝ ያለ ግለሰብ የወሊድ መቆጣጠሪያ ለመጠቀም የመጡ ሴቶች ቆዳ ስር የሎሊፖፕ መያዣ እንጨት ሲቀብር ነበር መባሉን ሰማን።
የ38 ዓመቱ ጆሴ ዳኒኤል ሎፔዝ የህክምና ትምህርትን ያልተከታተለ በሙያው ላይ ምንም ዓይነት ክህሎት ያልነበረው ነው ።
በዚህ ተግባሩ ታዲያ እርግዝናን ለመከላከል የመጡ ለ25 ሴቶች በዚህ መንገድ ያለፍላጎታቸው እንዲያረግዙ አድርጓል ነው የተባለው።
አቶ ሎፔዝ ያለምንም ሙያዊ ትምህርት በቪክቶሪያ ፣ ማራካይና ቬንዙዌላ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ውስጥ በድፍረት በሀኪምነት ሰርቷል።
ይህ በባለ ሙያተኞቹ አጠራር ኢምፕላንት በመባል የሚታወቀው የእርግዝና መከላከያ በክንድ ቆዳ ስር የሚቀበር እና ለረዥም ግዜያት እርግዝናን የሚከላከል ነው።
ታዲያ ደፋሩ ሎፔዝ ስለዚህ የእርግዝና መከላከያ የሚያውቀው አንድ ነገር ቢኖር በክንድ ስር መቀበሩን ብቻ ይመስላል።
የሎሊፖፕ ከረሜላ መያዣ የፕላስቲክ እንጨቶችን እርግዝናን የሚከላክል ኢምፕላንት ነው እያለ የበርካቶችን ጓዳ አመሰቃቅሏል።
የዚህ ጉደኛ ሰው ማጭበርበር የተጋለጠው በዋትስ አፕ በተባለ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ ላይ ስለ እርግዝና መከላከያ የሚያብራራ አንድ ሀኪም ብቅ ማለቱን ተከትሎ ነው።
ታዲያ ይህ ሀኪም በዚህ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ላይ በርከት ያሉ ቅሬታዎችን መቀበል ይጀምራል።
እሱ የሚያውቀው የእርግዝና መከላከያ ዘዴ እንዲህ አይነቱ አጋጣሚዎች ሊከሰቱበት እንደማይችል በማመን ጉዳዩን በጥልቀት ማጥናት ይጀምራል።
ታዲያ በመጨረሻም ሰውየው ትክክለኛውን የመከላከያ ዘዴ በሴቶቹ የክንድ ቆዳ ስር እንዳላስቀመጠው ሃኪሞችም ፖሊሶችም ይደርሱበታል።
ለዓመታት ሃኪም ነኝ እያለ ሲያጭበረብር የነበረው ሰውዬ ታዲያ ከህግ ለማምለጥ ተደብቆ ቢቆይም የኋላ የኋላ ግን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል ሲል ሜትሮ ኒውስ አስነብቧል።
ጉዳዩን ያጋለጠው የማህፀን ሀኪምም ግለሰቡ ይሰራበት በነበረው ሆስፒታል ውስጥ አገልግሎቱን ያገኛችሁ እህቶቻችን ሁሉ የህክምና ምርመራን አድርጉ ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-05-10
