ከመላው ዓለም የተወጣጡ ከ600 በላይ የንግድ ተቋማት ኃላፊዎችና ኢንቨስተሮች የሚሳተፉበት “ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023” ፎረም ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ከሚያዚያ 18 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄደው ፎረም “በኢትዮጵያ ኢንቨት በማድረግ በልጽጉ - ማራኪ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሏት ምድር” በሚል መሪ ሃሳብ ነው፡፡
በፎረሙ ከመላው አለም የተወጣጡ ኢንቨስተሮች፣ የንግድ ተቋማት ሃላፊዎች፣ የፖሊሲ አውጪዎችና ስራ ፈጣሪዎች የሚታደሙበት መሆኑም ታውቋል።
መርኃ ግብሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኢትዮ ቴሌኮም ዋና አጋር በመሆን አንዳዘጋጁት የተገለፀ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ የፎረሙ ህጋዊ የጉዞ አጋር መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ፈሰስ ሊደረግ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
ፎረሙ በሀገሪቱ ያሉትን የማምረቻ ዘርፍ፣ የግብርና፣ ኢነርጂ፣ አይሲቲ፣ የጤና ፣ትራንሰፖርትና ሎጀስቲክ፣ ቱሪዝም እና ሌሎች በማበብ ላይ የሚገኙ ዘርፎችን ያስተዋውቃል ተብሎ እምነት ተጥሎበታል፡፡
ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023 ለሁሉም ኢንቨስተሮች ፣የንግድ ተቋማት መሪዎች ፣ፖሊሲ አውጪዎች እና በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ማወቅ ለሚፈልጉ ስራ ፈጣሪዎች ክፍት መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
በናርዶስ ታምራት
2023-04-25
