ሀገሬ ቲቪ

አምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ

አምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ ዛሬ ግንቦት 03/2014 ዓ.ም ተካሔዷል በጉባዔው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የመንግሥት እና የግል ተቋማት እንዲሁም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እና ሌሎች እንግዳዎች ተሳታፊ ነበሩ። የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ የለውጥ መዕበል በነገሰበት ዘመን የነገውን የፍይናንስ ዘርፍ እንደገና መቅረጽ በሚል ጭብጥ ስር ፖሊሲዎችን እና አሰራሮችን መፈትሽ በሚል መሪ ቃል ጉባዔው ተካሒዷል።

የሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ በተለይም አገልግሎት አሰጣጡ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም ያሉት የአይካፒታል ኢኒስቲቲዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ገመቹ ዋቅቶላ ጉባዔው እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት እና ልምድ ለመቅሰም ጠቃሚ ነው ብለዋል። የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ አላማው በአጠቃላይ እሴት ሰንሰለቱ ላይ ባሉ እና በኢትዮጵያ እንዲሁም በአህጉሪቱ ውስጥ በፋይናንሱ ዘርፍ ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ወሳኝ ዘርፎች በሙሉ በተውጣጡ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች ፣ የባንክ ባለሙያዎች፣ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች ፣የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የመንግሥት ኃላፊዎች መካከል በርካታ አካላትን ያሳተፈ ውይይት መፍጠር ነው።

በፋይናንስ ዘርፉ በኛም ሀገር ሆነ በሌሎች ሀገራት የባለሙያ ዕጥረት የሚታይ ነው ያሉት ደግሞ የተመሰከረላቸው የሒሳብ እና ኦዲት ባለሙያዎች ማኀበር የሀገር ውስጥ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዮዲት ካሳ ናቸው። ይህን ችግር ይህን የባለሙያ ዕጥረት ለመቅረፍ ከገንዘብ ሚንስቴር ጋር የተጀመረ ፕሮጀክት መኖሩን ተናግረዋል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-05-11