ኢንዶሚ ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው ተባለ፡፡
በካንሰር የመያዝ እድልን የሚጨምር ንጥረ ነገርን ይዟል በተባለው ኢንዶሚን ኑድልስ ላይ የተለያዩ ሀገራት ምርመራ ማድረግ ጀምረዋል ሲል አዲስ አድማስ ጋዜጣ አስነብቧል፡፡
ማሌዥያና ታይዋን በኢንዶሚን ላይ “ኢቲሊን ኦክሳይድ” የተባለውን ካንሰር አምጪ ንጥረ ነገር በማግኘታቸው ምርቶቹን ከገበያ ላይ እንዲሰበሰቡ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በበኩሉ፣ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ ከውጪ ሀገር የሚገባ የኢንዶሚን ኑድልስ ምርት የሌለ መሆኑን እና በአገር ውስጥ የሚመረትና በባለስልጣኑ ቁጥጥር የሚደረግበት ምርት መኖሩ ተነስቷል፡፡
ጉዳዩ እንደተሰማ በዚሁ የአገር ውስጥ ምርት ላይ ምርመራ መደረጉን የገለፀው ባለስልጣኑ በምርቱም ላይ የተባለውን ዓይነት ለጤና ጎጂ የሆነ ንጥረ ነገር አለመገኘቱን አመልክቷል፡፡
በብሩክታዊት አስራት
2023-05-05
