ሀገሬ ቲቪ

የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌይ

በሙሉ ስሙ ነስታ ሮበርት ማርሌይ ይሰኛል። የተወለደው ከመካከለኛ እድሜ ነጭ የባህር ኃይል መኮንን እና ከ18 አመት ጀማይካዊ ጥቁር በፈረንጆቹ 1945 በገጠራማዋ ሴንት አን ፓሪሽ በጀማይካ ነው። በዘጠኝ አመቱ ወደ ትሬንች ከተማ ሄዷል።
በዚያም ከበኒ ዋይለር እና ፔተር ቶሽ መገናኘት ችሏል። በሙዚቃ ላይ መሳተፍ የጀመረው ማርሌይ በ14 አመቱ ሙዚቃ ለመስራት በሚል ትምህርቱን አቋርጧል። በዚያው ወቅት ጀማይካ አስገራሚ የሙዚቃ ፈጠራ ጊዜ ውስጥ ነበረች። በደሴቷ ሃገር ጀማይካ ትራንዚስተር ሬድዮዎች ብሄራዊ ሬድዮዎችን ያሰራጩ ነበር።

በጊዜው በመንግስት የሬድዮ ጣቢያዎች የአሜሪካ ሙዚቃዎች ተደራሽ መሆን ችለዋል። የተለያየ አይነት ስልት የተቀላቀለባቸው ሙዚቃዎች ይደመጡ የነበረበት ጊዜ ነው። በትሬንች ከተማ ቦብ ማርሌይ ከፒተር ቶሽ እና ቡኒ ዋይለር የቮካል ቡድን መስርተዋል። እስከ 1960ዎቹ ሬጌ የራሱን የተለየ ቅርጽ አልያዘም። በጀማይካ ሬጌ ተደማጭ ስልት እየሆነ ባለበት በዚሁ ጊዜ ቦብ ማርሌይ፣ ፔተር ቶሽ እና ቡኒ ዋይለር ዋይለርስ (The Wailers) በመባል በቡድን መጫወትን ተያይዘዋል።
ዋይለርስ በ1970ዎቹ የደሴቷ ሃገር ቅጅዎች ለአለም በመድረሳቸው የአለምን ትኩረት ‘Catch a Fire’(1972) እና ‘Burnin’(1973) በተሰኙ አልበሞቻቸው ማግኘት ችለዋል። የዘመኑ እውቅ ጊታሪስት ሙዚቀኛ ኤሪክ ክላፕተን ከአልበማቸው ለፖፕ ስልት የቀረበውን ‘I Shot The Sheriff’ ን በመጫወት የቡድኑን ስም እውቅና እንዲያገኝ አድርጎታል። እ.ኤ.አ በ1974 ቶሽ እና ዋይለር ከቡድኑ በመልቀቃቸው የቡድኑን ዋና ቦታ መያዝ ችሏል። እውቅናውም ከፍ ማለት ጀምሯል። ማርሌይ ቡድኑ በጥንካሬው እንዲቀጥል ማድረግም ችሏል።

በ1970ዎቹ መጨረሻ Exodus (1977)፣Kaya (1978) እና Uprising (1980) የተሰኙ አልበሞችን አውጥቷል። የማርሌይ ስራዎች የግል እውነቱን በአደባባይ የሚገልጹ መሆናቸው እና በአዲስ ስልት በመቀንቀናቸው ተወዳጅነትን እያተረፉ መጥተዋል። በዚህም ፖለቲካዊ ሰው ተደርጎ እንዲታሰብ አድርጎታል። በፈረንጆቹ 1976ም ከግድያ ሙከራ ተርፏል። ማርሌይ በፈረንጆቹ አፕሪል 1978 የጀማይካ የፖለቲካ አንጃዎችን ለማስታረቅ በሚል የኮንሰርቱን ስም ‘One Love’ ሲል ጠርቷል።
ቦብ ማርሌይ ስራዎቹ በህይወት ከነበረበት ይልቅ ካለፈ በኋላ ይበልጥ ተወዳጅ ሆነዋል። የጀማይካ መንግስትም የክብር ሽልማት ሸልሞታል። በዛሬዋ እለት ከዛሬ 41 አመታት በፊት ነበር በካንሰር ምክንያት በ36 አመቱ ያረፈው። ዛሬም ግን ሙዚቃዎቹ ከነተወዳጅነታቸው አሉ።

በአብርሃም በለጠ
2022-05-11