የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎታቸው እያደገ መምጣቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለፀ።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ መሳብ መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የአስር በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑ ተነግሯል፡፡
168 ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው በግብርና፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በኢነርጂ፣ ቱሪዝምና በሌሎችም የኢንቨስትመንት አማራጮች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍስስ የቅድመ ተግበራ ሥራቸውን አጠናቅቀው ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑም ተጠቁሟል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ‘’ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2023 ፎረም" በሚል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው ዓለማቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ከተለያዩ የውጭ አገራት ከመጡ ባለሃብቶች ጋር ሥምምነት መፈረሙን ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
ባለሃብቶቹ ከህንድ፣ ከቻይና ከኬንያና ከሌሎችም አገራት የመጡ ሲሆን 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ሥምምነት መደረጉንም ጠቁመዋል።
በብሩክታዊት አስራት
2023-05-13
