የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ከዛሬ ጀምሮ በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው፡፡
የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ከዛሬ ረቡዕ ጀምሮ ለሰባት ቀናት የሚቆይ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
አምባሳደር ሐመር በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመው እና ባለፈው ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የተፈረመውን ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ስምምነት አተገባበርን በተመለከተ በአዲስ አበባ እና በመቀለ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሏል።
በጂቡቲ ቆይታቸው ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መግለጫው አመልክቷል።
በናርዶስ ታምራት
2023-05-31
