ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ፈር ቀዳጅ ሴት እውቅና ተበረከተላቸው፡፡
ፕሬዝዳንቷ በቤልጂየም ፓርላማ በተካሄደውና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች አመራር ሴቶች በተገኙበት የሴት ፖለቲካ መሪዎች ድርጅት ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ነው እውቅናው የተበረከተላቸው።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ጨምሮ ከዚህ በፊት በተመድ ውስጥ በተለያዩ የስራ ዘርፎች በነበራቸው ከፍተኛ የኃላፊነትና የመሪነት ቦታዎች ፈር ቀዳጅ በመሆናቸውም ጭምር ያገኙት እውቅና መሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንቷ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ሽልማቱ ለብርቱዎቹ ሴቶች፣ በመጠለያ ጣቢያዎች ላሉት፣ ተማርከው ሕክምና ላይ ሆነው ሲጎበኟቸው የመማር ጉጉት እንዳላቸው ለነገሯቸው፣ ብቻቸውን ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነት ለተጣለባቸው እና ተስፋ ለሚሰጡን ባለ ተሰጥኦ የሀገሬ ሴቶች ይሁንልኝ ብለዋል።
በንግግራቸውም ሴቶች በሰላም እና ደህንነት ዙሪያ ስለሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች እና የሴቶች ውክልና በቁጥር ብቻ መተርጎም እንደሌለበት መናገራቸውን የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
10ኛው የሴት ፖለቲካ መሪዎች ድርጅት ዓመታዊ ጉባዔ በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ እና በቤልጂየም ፌዴራል ፓርላማ “ውክልና ወሳኝ ነው” በሚል መሪ ቃል በጋራ ተካሂዷል።
በብሩክታዊት አስራት
2023-06-10
