ሀገሬ ቲቪ

ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት ሊገጥማቸው እንደሚችል ተነገረ፡፡

ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተት ሊገጥማቸው እንደሚችል ተነገረ፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ባሳለፍናቸው ቀናት ከባድ ዝናብ በተከታታይ በማግኘት ላይ በሚገኙ ቦታዎች የአፈር ውስጥ እርጥበት መብዛት፣ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች አፈር መሸርሸርና የመሬት መንሸራተት ችግሮችን ሊያስከትል ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

እየቀጠለ ባለው ዝናብ በሚቀጥሉት ሰባት ቀናት በክረምት ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚኖርም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብና በመካከለኛው የሀገሪቱ ሥፍራዎች ላይ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እየተጠናከሩ የሚሄዱ ሲሆን፤ በአንጻሩ በሰሜንና በሰሜን ምሥራቅ ላይ አልፎ አልፎ ከሚኖረው መጠነኛ ዝናብ በስተቀር ደረቅና ሞቃታማ የአየር ሁኔታ እንደሚያመዝን በመግለጫው አስታውቋል።

ባሳለፍናቸው ቀናት በተገኙት የተሻለ እርጥበት የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን፣ የግጦሽ ሳር ልምላሜ፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምንጮችን ለማጎልበት ያግዛል ሲል አትቷል።

በአንጻሩ ከኦሮሚያ ክልል ሰሜናዊ የቦረናና ጉጂ ዞኖች፣ ከሶማሌ ክልል የፋፈን ዞን፣ ድሬዳዋ፣ ሀረሪ ክልል፣ አማራ ክልል የሰሜንና የደቡብ ወሎ፣ ዋግኽምራ እና የሰሜን ሸዋ ዞኖች ምስራቅና የደቡብ ትግራይ ክልል ዞኖችና ከአፋር ክልል ዞን አምሥት በተወሰኑ ስፍራዎቻቸው ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ።

በሌላ በኩል የሶማሌ ክልል ዞኖች፣ ከደቡብ ክልል የደቡብ ኦሞ እና የሰገን ሕዝቦች ዞኖች፣ ከአፋር ክልል አብዛኛው ዞኖች ደረቅ ሆነው ይሰነብታሉ ብሏል መግለጫው።

በብሩክታዊት አስራት
2023-06-14