የሰው ልጆች በዚህ ዓለም ሲኖሩ የሚያልፉበት አንዱ የህይወት መንገድ ነው፤ ጋብቻ።
ዳግም የመወለድ፤ የሁለተኛው ምዕራፍ የህይወት ጉዞ ጅማሬም ነው።
ታዲያ ይህንን የህይወት ምዕራፍ ጅማሮ እነደየ ሀገሬው ባህል እና ወግ የቻለ ድል አድርጎ ደግሶ፤ እንደው እሱስ ይቅርብኝ ያለ ወዳጅ ዘመድ ሰብስቦ እወቁልኝ አሁን ሙሉ ሰው ሆኛለው ይላል።
እንዲህ ያሉ የጋብቻ ማክበሪያ መድረኮች ወይም ሰርጎች ሳይተሩ በሰርጎ ታድመው ምግብ እና መጠጡን የሚካፈሉ ድንኳን ሰባሪዎች አያጣቸውም።
እኛም ታዲያ ከወደ ከወደ አሜሪካዋ አሪዞና ግዛት የሰማነው የአንድ ፖሊስ ድንኳን ሰበራ ግርም አደረገን እና ልናጋራችሁ ወደድን።
ሰውየው ድንኳን ሰበራ የተገኘባቸው ሰርጎች ላይ በእኛ ሀገር እንደለመድናቸው አይነት ድንኳን ሰባሪዎች በልቶና ጠትቶ ብቻም አይደለም የሚመለሰው፤ ለሙሽሮቹ የመጡ ስጦታዎችን በእጁ ይዞ ከሰርጉ መሀል ሹልክ ብሎ ይመለሳል።
የ54 ዓመቱ የቀድሞ የፖሊስ አዛዥ ባዶ እጁን በታደመባቸው ሰርጎች ላይ ለሙሽሮቹ የመጡ ስጦታዎችን እያማረጠ ይሰርቅ ነበር ነው የተባለው።
ግለሰቡ ከአንድ ሰርግ ቤት ውስጥ ለሙሽሮቹ የመጣን የሰርግ ስጦታ ይዞ ሲወጣ የሚያሳይ በደህንነት ካሜራ የተቀረፀ ምስል ይፋ ሆኗል።
ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር አውሎ የስርቆት ወንጀም መፈፀም የሚል ክስ ለመመስረት ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ግለሰቡ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት በመኪናው ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ መገኘቱን ተከትሎ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራወችን እያደረኩኝ ነው ብሏል።
ግለሰቡ ድንኳን ከሰበረባቸው ሰርጎች ላይ እስከ 6 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር የሚያወጡ የስጦታ እቃዎችን ሰርቆ የግሉ አድርጓል ነው የተባለው።
ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ ከአካባቢው ከሰባት በላይ በሆኑ ሰርጎች ላይ ለደረሰው የስጦታችን ተሰረቀ ጥቆማ ተተያቂ ሳይሆን አይቀርም።
ግለሰቡ ግን በሰርጎቹ ላይ መታደሜ ስነስርዓቱን ለመከታተል እንጂ ለሌላም አይደለ ባይ ነው። ከደህንነት ካሜራ የተገኘው ምስል ግን ይህንን አይልም።
ግለሰቡ እንደ ምዕራባውያኑ የዘመን ቀመር ከ1994 ጀምሮ እስከ 2015 ድረስ በአካባቢው በምክትል ፖሊስ አዛዥነት፤ ጡረታ ከወጣ በኋላ እስከ 2017 ድረስ ደግሞ በተጠባባቂ ኦፊሰርነት ሲያገለግል ቆይቷል።
ዘገባው የአሶሼትድ ፕረስ ነው።
በሳምሶን ገድሉ
2022-05-11
