ኢትዮጵያ ለአፍሪካ በሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
አቶ ደመቀ ከአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጂን ካሴያ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
በውይይቱም በአዲስ አበባ የተገነባው አዲሱ የአፍሪካ ሲዲሲ የዋና መቀመጫ ሕንጻ በአፍሪካ የጤና አጀንዳ ለማራመድ የሚያስችል ዐብይ ፕሮጀክት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ማዕከሉ እያከናወናቸው ላሉ ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።
የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጂን ኬሲያ የኢትዮጵያ መንግሥት ለማዕከሉ እያደረገ ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አፍሪካ ሲዲሲ ለአባል አገራት አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ መስጠቱን እንደሚቀጥል መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል የአፍሪካ ሕብረት ገለልተኛ የጤና ተቋም ሆኖ እ.አ.አ 2016 መቋቋሙ የሚታወስ ነው።
በብሩክታዊት አስራት
2023-07-04
