ፌዴሬሽን ምክር ቤት አዲሱ ክልል እንዲደራጅ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት በዛሬው ቀጣይ ዉሎው የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተካተቱበት «የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል» በሚል ስያሜ አዲስ 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ቀድሞ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይኖሩ የነበሩ የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባካሄዱት ሕዝበ ውሳኔ በአንድ ክልል የመደራጀት ፍላጎታቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በአንድ ክልል እንዲደራጁ በዛሬው እለት ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ ወስኗል፡፡
«የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል» በሚል በአዲስ የተደራጁት በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጎፋ፣ በጌዲዮ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በኮንሶ ዞኖችና በደራሼ፣ በቡርጂ፣ በአማሮ፣ በኧሌና በባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ሕዝቦች ናቸው፡፡
ቀድሞ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል ውስጥ የነበሩ የሀድያ፣ የሀላባ፣ የከምባታ ጠምበሮ፣ የስልጤ፣ የጉራጌ ዞኖችና የየም ልዩ ወረዳ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚቀጥሉ ይሆናል።
አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የውሳኔ ሀሳቡ እንዲጸድቅ አቅርበው በሙሉ ድምጽ ደግፎ ማፅደቁን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።
በሙሉጌታ በላይ
2023-07-05
