
43ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ዛሬ በኬንያ ናይሮቢ መካሄድ ጀምሯል።
ስብሰባው የሚደረገው “የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን ማፋጠን” በሚል መሪ ቃል ነው።
በስብስባው ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ዶክተር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋ፣ የሕብረቱ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና ዲፕሎማቶች፣ የሕብረቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ ቀጣናዊ የአፍሪካ ተቋማት ኃላፊዎች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ ነው።
በስብሰባው የአፍሪካ ቀጣናዊ ትስስር፣ የአፍሪካ ሕብረት ተቋማዊ ማሻሻያ፣ የአጀንዳ 2063 የቀጣይ 10 ዓመት የትግበራ እቅድ እና በሕብረቱ ስር ያሉ የተለያዩ አደረጃጀቶችን አፈጻጻም የተመለከቱ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።
የ2023 የአፍሪካ ሕብረት መሪ ቃል በሆነው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን የተመለከተ የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም ሪፖርት የሚቀርብ ሲሆን የሕብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የስራ አፈጻጸም ይገመገማል።
ከምክር ቤቱ ስብስባ ውጪ አምስተኛው የአፍሪካ ሕብረት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ተቋማት፣ ቀጣናዊ አደረጃጀቶች እና የአባል አገራት የአጋማሽ ዓመት ስብስባ ሐምሌ 9 ቀን 2015 በኬንያ ናይሮቢ እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
በብሩክታዊት አስራት
2023-07-13