የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፉት 9 ወራት የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 75 አመራርና ሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዴን እወቁልኝ ብሏል።
ከተለያዩ አካላት የቀረቡ 97 ጥቆማዎች እና 163 አቤቱታዎችን ተቀብዬ የማጣራት ስራ ሰርቻለሁ ያለው ተቋሙ የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙት አመራሮቹና ሰራተኞቹ ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መውሰዱን እና ቀሪ 87 የሚሆኑት ጉዳያቸው በዲሲፕሊን በመታየት ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።
እርምጃው የተወሰደው በተቋሙ ደንብ መሰረት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የገንዘብ ቅጣት፣ ከኃላፊነት ቦታ ማንሳት እንዲሁም እስከ ስራ ስንብት የሚደርስ እርምጃ መወሰዱ ታውቋል።
አብዛኛው የተቋሙ ሰራተኛ አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ጥቂቶች በህገ-ወጥ መንገድ አገልግሎቱን ለማግኘት ከሚፈልጉ ግለሰቦችና ደላሎች ጋር በመመሳጠር የሚሰሩ መኖራቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል አገልግሎቱ።
ቀርበው ከተጣሩ ጥቆማዎች መካከል በህገ-ወጥ መንገድ ቆጣሪ ማስገባት፣ ቆጣሪ ለማስገባት በሚደረገው ሂደት ጉቦ መጠየቅ፣ ደንበኛን በአግባቡ አለማስተናገድ፣ ያለበቂ ምክንያት ስራን ማዘግየትና ደንበኛን ማጉላላት፣ በአስቸኳይ የጥገና ስራ ደንበኞች ገንዘብ አዋተው እንዲከፍሉ ማስገደድ፣ ያለደረሰኝ የቆጣሪ ማስገቢያ ክፍያ መቀበል እና የመሳሰሉት በተደረገ የማጣራት ስራ የተገኙ ጥፋቶች ናቸው።
ተቋሙ “ብልሹ” ሲል የጠራውን አሰራር ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንና የድርጊቶቹን መንስዔዎች በጥናት በመለየት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ተነግሯል።
እንደ ተቋሙ ከሆነ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ አማራጭ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ጥቅም ላይ እያወለ እንደሆነና የደንበኞች አገልግሎት መመሪያ እንዲሻሻል መደረጉ የተሰማ ሲሆን ይህም ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የደንበኞችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ጉልህ ሚና አለው።
ተቋሙ የተለያዩ የቅሬታ ማስተናገጃ ስርዓቶችን ዘርግቷል። ደንበኞች በተዘረጉ የቅሬታ ማቅረቢያ ስርዓቶች ቅሬታቸውን፣ ጥቆማቸውን እና ሃሳባቸውን ማቅረብ ይችላሉ ተብሏል።
ከዚህ በፊት ሁሉም የተቋሙ ሰራተኞች ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ መደረጉን ተቋሙ አስታውሷል።
በማኑዋል የነበረው የሀብት ማስመዝገብ አሰራር ወደ ዲጂታልም ተቀይሯል።
ከዚህ በተጨማሪም የማዕከላት ኃላፊዎች ምደባ ሥነ-ምግባርንና ችሎታን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ለማድረግ አሁን ያለውን አሰራር በማሻሻል የምደባ መመሪያ ተዘጋጅቷል።
ደንበኞችም ህግን ብቻ መሰረት አድርገው አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸውና ችግር ሲያጋጥማቸውም ተቋሙ በዘረጋው የቅሬታ ማስተናገጃ ስርዓት መሰረት ቅሬታቸውን ማቅረብ እና መብታቸውን ማስከበር፣ሙሰኞችን ማጋለጥ እንደሚገባ በተቋሙ ተመክረዋል።
በመቅደስ እንዳለ
2022-05-12
