በጋምቤላ መምህራን ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚፈተኑ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ላይ አጋጥሞ የነበረውን የጤና እክል ምክንያቱ ምን እንደሆን ለማጣራት ፖሊስ ምርመራ መጀመሩ ተገለፀ።
በሚመገቡት ምግብ ላይ የመመረዝ አልያም የምግብ መበላሸት መሆኑን በህክምና ከሚደረገው ምርመራ ጎን ለጎን የክልሉ ፖሊስ ሶስት የምግብ አዘጋጆችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ ገልፀዋል።
የህክምናና የፖሊስ ምርመራው ሲጠናቀቅም ለህዝብ ይፋ ይደረጋል መባሉን የጋምቤላ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በማኀበራዊ ገጹ አስፍሯል።
ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሚፈተኑ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ተፈታኝ ተማሪዎች የጤና እክል ገጥሟቸው በጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደነበር ይታወሳል።
በሙሉጌታ በላይ
2023-08-04
