የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዙር ድርድር ያለስምምነት ተጠናቋል፡፡
ላለፉት ሁለት ቀናት በካይሮ የተካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን የግብጽ ሚድያዎች ዘግበዋል።
የግብጽ መንግሥት በድርድሩ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ምንም አይነት የአቋም ለውጥ ባለማድረጉ ድርድሩ ሳያፈራ ቀርቷል ሲል ከሷል።
ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሦስቱም የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሃዊ ተጠቃሚ በሚሆኑበት አግባብ ስምምነቶች እንዲደረጉ በተደጋጋሚ ግፊት እያደረገች ትገኛለች።
የቀጣዩ የህዳሴ ግድብ ድርድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በመስከረም ወር በአዲስ አበባ ይደረጋል ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ድርድሩ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ድርሻ ማስጠበቅ እንደተጠበቀ ኾኖ "ፍትሃዊ" እና "ምክንያታዊ" መርሆዎችን ባከበረ መልኩ እንዲቋጭ ጥረት እንደምታደርግ አስታውቆ እንደነበር አይዘነጋም።
በሳምሶን ገድሉ
2023-08-29
