ሀገሬ ቲቪ

ለገበያ የቀረቡት ያረጁ ጫማዎች

ያረጁ የተበጣጠሱ ቁሶች፣ መገልገያዎች መጨረሻቸው የቆሻሻ መጣያ ነው። እነዚህን አይነት መገልገያዎች ታዲያ በቅንጡ ምርቶች መደብር ውስጥ ቢያገኟቸውስ። መቼም እንዲህ አይነቱ ነገር እብደት ነው ሊያሰኝ ይችላል።

ለወትሮ ወደ ቡቲክ የሚያቀና አንድ ሰው በዘመነኛው አጠራር የዘነጡ ወይም የግዜውን ፋሽን የተከተሉ አልባሳትን ገዝቶ ይመለሳል። በእነዚህ የቅንጡ አልባሳት እና መጫሚያዎች መሸጫ ውስጥ በየቆሻሻ መጣያው የተጣሉ ጫማዎች ተሰቅለው እየተቸበቸቡ ነው መባሉን ሰምተናል። ባሌንሲጋ በአሜሪካ የሚገኝ ቅንጡ አልባሳት እና መጫሚያዎችን ለገበያ የሚያቀርብ ዝነኛ ኩባንያ ነው።

ታዲያ ይህ ኩባንያ አሁን በራሱ ስም ያመረታቸውን ለተመልካች ግርምትን ያጫሩ የተጣሉ የሚባሉ ጫማዎችን ለገበያ አቅርቧል። ኩባንያው እነዚህን ጫማዎች ለመግዛት ለሚመጣ ሰው ያቀረበው ዋጋ ደግሞ በይበልጥ ነገሩን መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል። አስቀያሚ ጫማዎቹን የግሉ ማድረግ የሻተ 1,850 ዶላር መክፈል ይጠበቅበታል ብሏል።

ኩባንያው ታዲያ 100 ጥንድ ጫማዎችን ብቻ ለገበያ ማቅረቡን አስታውቆ ይህ ታሪካዊ እድል አያምልጣችሁ እያለ ይገኛል። እኚህ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ፋሽን ሆነው በርካቶች የዘነጡባቸው የሸራ ጫማ አይነት የመሰሉ አሮጌ ጫማዎች የተለያየ ተቃውሞን እያስተናገዱም ይገኛሉ።

በማህበራዊ መገናኛ ዘዴው ቲውተር ላይ አንድ ግለሰብ ጫማው ከቆሻሻ መጣያ ከምታገኘው ጫማ የሚለየው በሶሉ ላይ የብራንዱ ስም በጉልህ በመጻፉ ብቻ ነው ሲል ወርፎታል።

እንዲህ አይነቱን ምርት ለገበያ ከማቅረቡ በፊት የማህበራዊ የዳሰሳ ጥናቶችን ማድረግ ነበረበት ሲሉ ኩባንያውን የመክሩም አልታጡም። በዚህ ሁሉ መሀል ግን የኦንላይን ቡቲኩ ባሌንሲጋ ጫማዎቹን የወደዳችሁ ኑ እድሉን ተጠቀሙ እያለ ይገኛል

በሳምሶን ገድሉ
2022-05-12