የሰው ልጅ ጥሮ ግሮ ለዘመናት ያፈራውን ጥሪት በአንድ ጀምበር ዶግ አመድ ያደርጋል ። የማይራራው የ እሳት አደጋ። ከጥንቃቄ ጉድለት እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች በተደጋጋሚ ሲከሰት ይስተዋላል ። ትላንት በመዲናችን አዲስ አበባ በተለምዶ ኢንዱስትሪ መንደር በመባል በሚጠራው አካባቢ ምሽት ላይ ከፍተኛ የእሳት አደጋ የተነሣ ሲሆን ቃጠሎው ተባብሶ በበርካታ ሼዶችና መጋዘኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ።
የአዲስ አበባ የእሳት አደጋ መኪኖችና አባላት በቦታው የተገኙ ቢሆንም አደጋው የደረሰበት ቦታ አመቺ ባለመሆኑ እሳቱን ለማጥፋት ረጅም ሰዐት እንደወሰደም ተገልጻል ። ስለደረሰው አደጋ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በ እሳትና አደጋ ስራ አመራር ኮሚሺን የ ህዝብ ግንኙነት ባለሞያ አቶ ንጋቱ ማሞ '' አደጋው ትናንት ከምሽቱ 3 ሰዓት የተነሳ ሲሆን በእሳት አደጋ ሰራተኞች እንዲሁም በ አካባቢው ነዋሪዎች ርብርብ ከለሉቱ 10 ሰዓት መቆጣጠር ተችሏል።'' ብለዋል።
ለማጥፋት 8 ሰዐታትን በፈጀው አደጋ በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እየተጣራ ሲሆን በሰው ህይወት ላይ እሳቱን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ከተፈጠሩት ቀላል አደጋዎች ውጪ ሌላ የደረሰ ጉዳት የለም።
ከ ቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመዲናችን አዲስ አበባ ብሎም በ አንዳንድ ክልሎች ከፍተኛ የእሳት አደጋ እየተሰትዋለ ሲሆን። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 277 አደጋዎች ሲያግጥሙ ከደረሰው የንብረት ጉዳት በተጨማሪ አንድ መቶ አራት ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን አቶ ንጋቱ ተናግረዋል ። የነዚህ አደጋዎች መበራከት መንሴኤው ምን ይሆን ስንል ለጠየቅናቸው ጥያቄ አቶ ንጋቱ በአብዛኛው የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑን ነግረውናል።
እሳት አደጋ ለነገ አይልም ከንብረትም አልፎ የሰው ህይወት ላይ የሚያደርስው አደጋ አይተኬ ነውና ጥንቃቄ አይለየን መለዕክታችን ነው ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-05-13
