የዓለም ባንክ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሀገራት የሚላከው ገንዘብ በዚህ ዓመት 4 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያድግ ትንበያውን አሳውቋል። ትንበያው በገንዘብ ሲተመን 630 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል።
ከሩሲያ ጋር ሁለት ወር በተሻገረ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ዩክሬን በዓለም ባንክ ሪፖርት ተካታለች። ዩክሬን ከአውሮፓ እና ከመካከለኛው እስያ የሚገኙ ዜጎቿ ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ሀገራቸው ይልካሉ።
በዚህ ዓመት ታዲያ ወደ ሀገሯ የሚገባው ዶላር ከ20 በመቶ በላይ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። በተቃራኒው ሩሲያ የገንዝብ ምንጭ የሆነቻቸው ሀገራት ወደ ሀገራቸው የሚገባው ገንዘብ እንደሚቀንስባቸው ነው የድርጅቱ ሪፖርት የሚያሳየው። ሀገሪቱ በጦርነት መጠመዷ ደግሞ እንደምክንያት ተቀምጧል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በብዙ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እና የፋይናንስ ተቋማት እየተገለጸ ያለው ነገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ነዳጅን ጭምሮ የሸቀጦች ውድ መሆን ነው። የዓለም ባንክም ታዲያ ዜጎች ወደ ሀገራቸው የሚልኩት ገንዘብ ማሽቆልቆሎች፣ ከምግብ፣ ማዳበሪያ እና የነዳጅ ዘይት ዋጋ መጨመር ጋር ተዳምረው ለምግብ ዋስትና ሥጋት ሊጨምሩና በብዙዎቹ ሀገሮች ድህነትን ሊያባብሱ ይችላሉ ብሏል።
የድርጅቱ ሹም የሆኑት ሚካል ሩትኮውስኪ እናደተናገሩት ከሆነ ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ሲሉ የጠሩትን ድርጊት ፈጽማለች። በዚህም ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ተፈጥሯል። በተጨማሪም የፈላሲያን ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።
“ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያደረገቸው ወረራ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ፈጥሯል። የፈላሲያን ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል። የዓለም ኢኮኖሚ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ መፈተኑን ቀጥሏል” ብለዋል
በማዕከላዊ እስያ ዩክሬናውያንን እና ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም በጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ የተጎዱትን ጨምሮ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ለመታደግ የማኅበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞችን ማሳደግ እንደሚገባ በዚሁ ሪፖርት ተነስቷል። በተጨማሪ ሰዎችን ከምግብ እጦት ሥጋት እና ድህነት መጨመር መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነውም ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2021 ከውጭ የሚላክ የውጭ ምንዛሪ ገቢ አሊያም ሬሚታንስ በላቲን አሜሪካ እና በካሪቢያን 25.3 በመቶ ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት 14.1 በመቶ ፣ በአውሮፓ እና መካከለኛ እስያ 7.8 በመቶ ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ 7.6 በመቶ እንዲሁም በደቡብ እስያ 6.9 በመቶ እንደነበር የዓለም ባንክ በጉዳዩ ላይ ያወጣው ዝርዝር መግለጫ ያሳያል። ባለፈው ዓመት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ካገኙ ሀገራት መሀከል።
ህንድ፣ ሜክሲኮ (ቻይናን በመተካት)፣ ቻይና፣ ፊሊፒንስ እና ግብፅ ናቸው። ሜክሲኮ ቻይናን ልትበልጥበት የቻለችው አብዘኛው ዜጎቿ ሀገራቸውን ጥለው በመሰደድ ጉልበታቸው በሰው ሀገር ላይ በማፍሰሳቸው ነው።
በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ላሉ ታዳጊ ሀገራት የሚላከው የገንዘብ መጠን በ2021 በ7.6 በመቶ ወደ 61 ቢሊዮን ዶላር አድጓል።
በዩክሬን ያለው ጦርነት ከድንበር ተሻጋሪ የገንዘብ ልውውጦች ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓቶች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ሩሲያ ስዊፍት ከተሰኘ የገንዘብ መላላኪያ ሥርዓት እንዳትጠቀም መገለሏን ዘገባው እንደአብነት አንስቶታል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-05-13
