ሀገሬ ቲቪ

‹‹በአፍሪካ ኅብረት ግቢ ውስጥ ለተፈጠሩ ክስተቶች ኢትዮጵያ ልትወቀስ አይገባም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ከ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጋር በተያያዘ ከሚነሱ ቅሬታዎች ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያ ልትወቀስ አይገባም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኅብረቱ ቅጥር ግቢና አዳራሽ ውስጥ በተፈጠሩ ማናቸውም ክስተቶች ሁሉ መጠየቅ ያለበት የአፍሪካ ኅብረት መሆኑንም ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ሚና እንግዶችን ተቀብሎ የአፍሪካ ኅብረት በር ማድረስ ነው፣ ነገር ግን እንግዶች ወደ ኅብረቱ በርና ቅጥር ግቢ ከደረሱ በኋላ ቀሪው ጉዳይ የኅብረቱ ነው መሆኑም ተነስቷል ሲል ሪፖርተር አስነብቧል፡፡

ከየካቲት 9 እስከ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በኅብረቱ ጉባዔ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ከገቡ ተሳታፊዎች፣ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ልዑካንና በሌላ ተሳታፊ አገር ልዑካን መካከል በኅብረቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ አለመግባባት መፈጠሩ ይታወቃል።

በተመሳሳይ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ፣ ‹‹ወደ ስብሰባው እንዳልገባ የመከልከል ሙከራ ተደርጎብኛል፣ ኢትዮጵያ አላከበረችኝም›› የሚል ወቀሳ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

በብሩክታዊት አሥራት
2024-02-26