ሀገሬ ቲቪ

መዋቢያ አስቀያሚ ያደረጋት ሴት

በርካታ ሴቶች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን መሰረት ያደረገ መዋቢያ ወይም ሜካፕን ይተቀማሉ። ታዲያ ሩጫ በበዛባት ዓለም ውስጥ በየቀኑ የቅንድብን እድገት እና መስተካከል መከታተል ለበርካታ እህቶቻችን አድካሚ ነው ይባላል።

ለዚህም ይመስላል ዘመኑ ረዘም ላለ ግዜ መቆየት የሚችል ቅንድብ ላይ የሚደረግ መዋቢያን ማምጣቱ። በዚህ የመዋቢያ መንገድ እራሴን አሳምራለው ያለች እናት መጨረሻዋ አላማረም መባሉን ሰምተናል። የተሰራችው ቋሚ የፊት ገፅታ ማስዋቢያ ማይክሮ ብላዲንግ አስቀያሚ ገጽታን እንድትላበስ አድርጓታል።

የ37 ዓመቷ የሁለት ልጆች እናት የዕለት ውሎዋ፣ ከልጆች መንከባከብ ጋር ተጨምሮ የተስተካከለ የፊት ገጽታ ኖሯት ከቤት እንድትወጣ አልሆንልሽ ይላታል። በተለይ በየቀኑ ከቤት ከመውጣቷ በፊት የቅንድቧን ሁኔታ ለማስተካከል መሞከሩ ቢያለፋት ቋሚ መፍትሄ ስለመስጠት ታስባለች። ለዚህም ፍቱን መድሀኒት አድርጋ የወሰደችው ነገር ረዘም ላለ ግዜ መቆየት የሚችለውን ማይክሮ ብላዲንግ የተባለ የቅንድብ ማስዋቢያን መጠቀም ነው።

ታዲያ ውበቴን ይጠብቅልኛል ያለችው የቅንድም ማስዋቢያ ግን እንዳሰበችው አልሆነላትም፤ ይልቁኑም በፊቷ ላይ ሌላ አይነት ገጽታን እንድትላበስ አደረጋት እንጂ።

በመስታወት እራሴን ስመለከት ማመን አልቻልኩም ነበር ስትልም በሰዓቱ የተሰማትን ድንጋጤ ተናግራለች።

ነገሩ ይህንን መዋቢያ በአግባቡ መስራት በማይችል የውበት ባለሙያ በመሰራቷ የመጣ እንደሆነም ጨምራ ተናግራለች። ውበቴን እጨምርበታለው ብላ 493 ዶላር ከፍላ የተሰራችው መዋቢያ ይባሱኑም የገዛ ልጆቿ እንዲፈሯት ስላደረገባት የተሰማትን ሀዘንም አልደበቀችም።

የተበላሸ ቅንድቧን ለማስተካከል ታዲያ እሷ ካለችበት ግዛት 4 ሺህ በላይ ኪሎሜትሮችን አቋርጣ ወደ ካሊፎርኒያ መሄድ የግድ ብሏታል።

ደግነቱ ጉዳዩን ከማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ላይ ያገኘ አንድ አስዋቢ ግድ የለሽም እኔ ጋር ነይ ያለምንም ክፍያ የቀደመ ውበትሽን እመልስልሻለው ብሏታል።

ሲያጌጡ ይመላለጡ ይሉት ተረት ይሄንንስ አይደል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-05-13