አይደር ሆስፒታል በየሳምቱ 110 ለሚኾኑ ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ሕክምና እየሰጠ ነው አለ።
በመቐለ ዩኒቨርስቲ ሥር የሚገኘው ‘’የአይደር ስፔሻላይዝድ’’ ሆስፒታል በ 2000 ዓ.ም. ግንቦት ወር ነበር ወደ ሥራ የገባው።
ይህ ሆስፒታል በዓመት ከ ሦስት መቶ ሺሕ በላይ ተመላላሽ ታካሚዎችን የሚያስተናግድ፣ 17 ሺሕ የሚጠጉ ተኝተው የሚታከሙ ሕሙማንን ያገለግላል። ሆስፒታሉ በዓመት ከ 5 ሺሕ በላይ እናቶችን የማዋለድ አቅም አለው። ከዚህ ባሻገር ግን ‘’ለተሻለ ሕክምና’’ አዲስ አበባን ጨምሮ ከክልሉ ውጪ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች የሚላኩ ሕሙማንን ውጣ ውረድ እና እንግልት አስቀርቷል።
ከሦስት ዓመት በፊት በትግራይ ክልል ተከስቶ የነበረው ጦርነት አይደር ሆስፒታል የነበረውን አቅም እንዳሳጣው የሆስፒታሉ ዋና ክሊኒካል ዳይሬክተር እና የሕፃናት የነርቭ ሐኪም ‘’ዶ/ር አብርሃ ገ/ እግዚአብሔር’’ ለጣቢያችን ገልፀዋል።
ሆስፒታሉ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ በጦርነቱ ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸውን ሴቶች ሕክምና መስጠት ዋንኛው ነው። ዶ/ር አብርሃ እንደነገሩን ከኾነ፤ ‘’በባሕል በሕብረተስቡም ውስጥ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ የሚያስገባ ስለኾነ በርካታ የጾታዊ ጥቃት ሰለባ የኾኑ ሴቶች ወደ ሕክምና ተቋማት አይመጡም’’ ብለዋል።
በጣም ጥቂት ሴቶች ብቻ ወደ ሆስፒታሉ እንደሚመጡ ገልፀዋል። በሳምንት 80 ከፍ አለ፤ ከተባለ ደግሞ እስከ 110 የሚደርሱ ሴቶች ሕክምናን ሽተው የአይደር ሆስፒታልን ደጅ እንደሚረግጡ ነግረውናል።
የጦርነቱ ወቅት በርካታ ሴቶች ይመጡ እንደነበር ዶ/ር አብርሃ ያስታውሳሉ።
አሁን ላይ ቁጥራቸው ይነስ እንጂ የሚመጡት ታካሚዎች ከደረሰባቸው ጥቃት ጋር ተያይዞ የወሊድ አካላት ሕመም፣ ከወሲባዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎች፣ የጀርባ መቀጥቀጥ፣ የሥነ አዕምሮ ሕመም (posttraumatic stress disorder) ተጋላጭ እንደኾኑ ተናግረዋል።
ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በብዛት ወደሆስፒሉ እንደሚመጡ ተገልጿል። በየሳምንቱ ከሚታከሙት ከ 80 እስከ 110 የሚደርሱ ታካሚዎች ‘’ሁለት ሦስተኛ’’ የሚኾኑት ሳይሻላቸው በድጋሜ ወደ ሆስፒታሉ የሚመለሱ መኾናቸውን ዶ/ር አብርሃ ገልፀዋል።
‘’በቤተሰቦቻቸው ፊት ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች’’ ምንም እንኳን መኖሪያ ቀዬአቸው ሠላም ቢኾንም እንዳልተመለሱ ሰምተናል። የዚህን ምክንያት ዶ/ር አብርሃ ሲያስረዱ እንዲህ ዓይትነት ጥቃት የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ ጫን ከፍተኛ በመኾኑ ዳግም ቤተሰቦቻቸውን ማየት ስለሚከብዳቸው መኾኑን ተናግረዋል።
በደረሰባቸው የአስገድዶ መደፈር ልጅ የወለዱ በርካታ ሴቶች በክልሉ መኖራቸውን ገልፀዋል።
ምንም ገቢ ሳይኖራቸው ከራሳቸው አልፈው ልጆቻቸውን መመገብ ሳይችሉ ቀርተው ‘’ ተራብን እያሉ የሚመጡም አሉ’’ ብለውናል። ‘’ሕመሙ እና ሁኔታው የጤና ሕመም ብቻ ሳይኾን ኀብረተሰባዊ ቀውስ’’ መፍጠሩን የአይደር ስፔሻላይድ ሆስፒታል ዋና ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብርሃ ገ/ እግዚአብሔር ጠቁመዋል።
ችግሮቹን ለመቅረፍ ቢያንስ ሕክምና ካገኙ በኋላ ከ 30 እስከ 40 ሴቶችን ማስተናገድ ወደሚችል ‘’ሴፍ ሀውስ’’ ወደ ተሰኘ ማቆያ እንዲገቡ ይደረጋል። በመቐለ፣በአዲግራት፣ በሽሬ እነዚህ ማዕከላት አሉ። ይሁን እንጂ ከታካሚዎች አንፃር የሚቀበሏቸው ‘’ ኢምንት’’ ነው ሲሉ ዶ/ር አብርሃ ገልፀውታል።
በማዕከሉ ለሦስት ወር እንዲቆዩ በማድረግ የሥነ ልቦና ሕክምና፣ የሙያ ክሕሎት ትምሕርት እንዲያገኙ ይደረጋል።
ይህ ማዕከል ለበርካታ ሴቶች ተደራሽ አለመኾኑ ተግዳሮት ኾኖ መቀጠሉን ከሆስፒታሉ ሰምተናል። በመድኃኒት አቅርቦትም ቢኾን አይደር ሆስፒታል ‘’ከ 40 በመቶ’’ አልፎ እንደማያውቅ ተሰምቷል። ‘’ከፕሪቶሪያ የሠላም ስምምነት’’ በኋላ ያሉት እንቅስቃሴዎች የተሻሻሉ ቢኾኑም የመድኃኒት አቅርቦት ዛሬም ታካሚዎችን እና ሆስፒታሉን እየፈተነ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የሕክምና ተቋሙ ታካሚ የሚያስፈልገውን ሙሉ መድኃኒት ሰጥቶ የማይልክ መኾኑን ዶ/ር አብርሃ ነግረውናል።
በአጠቃላይ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች አክሞ የስነ ልቦና ጫናቸውን ለማቅለል፤ ሕክምናው ብዙ ሴክተሮች ወይም ዘርፎች አንድ ላይ ሊሳተፉበት የሚገባ መኾኑን ዶ/ር አብርሃ ያነሳሉ።
ሕክምናቸውን የሚከታተሉት ሁሉም ሴቶች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው መኾናቸውን የሆስፒታሉ ዋና ክሊኒካል ዳሬክተር ዶ/ር አብርሃ ገ/እግዚአብሄር "ለሀገሬ ቴቪ" ተናግረዋል፡፡
በየሳምንቱ ከሚመጡ 110 የሚጠጉ ሕክምና ፈላጊ ሴቶች አብዛኞቹ ሳይሻላቸው በድጋሚ ተመልሰው ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ መኾናቸውን ሰምተናል።
በበጣቢያው ሪፖርተር
2024-03-27
