ሀገሬ ቲቪ

ዘመን ተሻጋሪ ሕመም የተሸከሙት ሴቶች

በቅጽል ሥሟ ‘’ባርች’’ እያሉ ይጠሯታል።

የሚያውቋት እና የምታውቃቸው። እጅግ ተጫዋች እና ተግባቢ ነበረች የተባለችውን ባርች እኛ ስናገኛት ግን ይህ ባሕሪዋ ተለውጧል። ተጫዋቿ ባርች ጭምት ኾናለች።

የዚህ ባሕሪዋ መለወጥ ዋና ምክንያት ጥቅምት 23/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል የተነሳው ጦርነት እና ሕይወቷ ላይ ጥሎት ያለፈው ዛሬም ‘’ሊሽርላት ያልቻለ ቁስል’’ ነው።

በዚህ ጦርነት በትግራይ ክልል ብቻ ‘’በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ፆታዊ ጥቃት’’ ደርሶባቸዋል። በተመሳሳይ ጦርነቱ ወደ አማራ ክልል ሲሻገር በርካታ ሴቶች፣ እናቶች እና እህቶች የዚህ ጥቃት ሰለባ ኾነዋል።

‘’ባርችም’’ ታዲያ በጦርነቱ ወቅት ፆታዊ ጥቃት ደርሶባታል። ይህን አጋጣሚ እና ሁኔታ ወደ ሦስት ዓመታት ዞር ብሎ ማውራት ‘’ቀላል አይደለም አንደበትን ያስራል’’ ትላለች።

በጦርነቱ ወቅት ባርች ልጇን አስቀምጣ ከቧለቤቷ ጋር ‘’የትግራይን ልዩ ኃይል’’ ተቀላቅላ ተዋግታለች።

ይሁን እንጂ ‘’ጭና’’ በምትባል አካባቢ ላይ ተያዝኩ በወቅቱ ብዙ ወታደሮች ነበሩ ትላለች ሆድ በባሰው እና በተቆራረጠ ድምጿ።

በመሃል ግን መቀጠል አልቻለችም ትውስታዋን ልታወራው አልወደደችም፤ እንባ እና ሳግ ተናነቃት። ‘’ብቻ ብዙ ነገር አልፏል ቀኑ አልፋል፤ መርሳት ግን አይረሳም’’ አለችን። የደረሰባት ፆታዊ ጥቃት ‘’የእዕምሮ ሕመምተኛ’’ እንዳደረጋት ነግራናለች።

‘’እዕምሮዬን ስለሚያመኝ የኾነውን ነገር ማስታወስ ይከብደኛል ረጅም ሰዐት እያሰብኩ እና እያስታወስኩ ነው የማወራው’’ አለችን።

‘’ጦርነት ላይ ሳለን ባለቤቴ የልጄ አባት ተሰውቷል’’ ስትል ሌላኛውን ቶሎ የማይሽር ሕመሟን ነገረችን። ይህን ተደራራቢ ችግር ይዛ ኑሮዋን በመግፋት ላይ ሳለች ነበር ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች እየደገፈ እና እያገዘ ስለሚገኝ ‘’ሕውየት’’ ስለተባለ በጎአድራጎት ተቋም የሰማችው።

ይህ ተቋም በጦርነቱ ወቅት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና እናቶች መድኃኒት እና ሕክምና እንዲያገኙ ድጋፍ ያደርጋል። በተጨማሪ 50 ሺህ ብር እየመደበ ለእነዚህ እናቶች በመስጠት መተዳደሪያ የሚኾናቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ ዕድል ይከፍታል።

‘’የእነዚህ ሴቶች ስቃይ እና መከራ መመልከቴ ወደዚህ ሥራ እንድገባ አስገድዶኛል’’ ትላለች የተቋሙ መሥራች ‘’መሠረት ሓዱሽ’’ ቀሪ ሕይወታቸውን በሠላም ያሳልፉ ዘንድ የተቋሙን ስያሜ ‘’ሕውየት’’ እንደተባለ ነግራናለች። ትርጉሙም ‘’ማዳን፣ መፈወስ’’ ማለት ነው።

እኛም በዚህ ተቋም ግቢ ውስጥ በተገኘንበት ወቅት ልክ እንደ ‘’ባርች’’ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሌሎች ሴቶች ተመልክተናል።

በዚህ ሁለት ሦስት ዓመት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ታሪክ በተንቀሳቀሽ ምስል፣ በጽሑፍ ሰንደን ዓለም እንዲያውቀው፤ ሰው እንዲረዳው፣ ደጋፊ እንዲኾን እናስቀምጣለን ስትል ወ/ሮ መሠረት ነግራናለች። አንዱ የሕውየት በጎአድራጎት ተቋም ሥራ ይህ ነው።

እዚህ ችግር ውስጥ ያሉ ሴቶች ሕክምና አያገኙም በተጨማሪ ከፍተኛ የኾነ የመድኃኒት ዕጥረት ያጋጥማቸዋል። ‘’ለአንድ እናት 1ሺህ ብር አውጥታ መድኃኒት መግዛት ሌግዠሪ(ቅንጦት) ነው’’ ስትል ወ/ሮ መሠረት ትገልጻለች።

እነዚህ ሴቶች በገንዘብ አለማግኘት ምክንያት የታዘዘላቸውን መድኃኒት መግዛት እንደማይችሉ፤ ከአራት እና ከአምስት ወር በኋላ ሕመማቸው ጠንክሮ ሕይወታቸውን የሚያጡ ሴቶች ቁጥር ትንሽ እንዳልኾነ ‘’ሕውየት’’ ከተሰኘው ተቋም ሰምተናል።

ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በዚሁ የመድኃኒት እጥረት እና የዋጋው ውድ መኾን የማሕፀን ካንሰር ተጠቂ እናቶች፣የፌስቱላ ተጎጂዎች፣ የኤች አይቪ ታማሚዎች ቁጥር ከፍ እንዳደረገው ተገልጿል።

በተለያዩ የትግራይ ክፍሎች በመዘዋወር ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች እና ያሉበትን ሁኔታ እንደምታጠና ወ/ሮ መሠረት ሓዱሽ ነግራናለች። ለአብነት በደቡብ ትግራይ ‘’ ቦራ’’ የተሰኘች አካባቢ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸ 550 እናቶች ማግኘቷን እና ከነዚህ ውስጥ ሕክምና ያገኙት ‘’36 ብቻ’’ መኾናቸውን ማረጋገጧን ነግራናለች።

እኛም ይህንን ጉዳይ እንዴት እያያችሁት ነው ስንል የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊን ዶ/ር አማኑኤል ኃይለን ጠይቀን ነበር።

ከዓለም የጤና ድርጅት፣ የጤና ሚኒስቴር ጋር በመኾን በተሠራ ጥናት በክልሉ ካሉ ጤና ተቋማት 86 በመቶ በከፊል፤ 3 በመቶ የሚኾኑት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ መወደማቸውን ዶ/ር አማኑኤል ተናግረዋል። ይህ መኾኑ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ጨምሮ ለሌሎች ዜጎች የሕክምና አገልግሎትን መስጠት ፈታኝ እንዳደረገው ተናግረዋል።

‘’የዋን ስቶፕስ’’ ክሊኒኮችን በማቋቋም እነዚህን ሴቶች ለማገዝ እየሞከርን ነው ብለዋል። የሥነ ልቦናን ጨምሮ ሌሎች ሕክምና ይሠጣቸዋል ተብሏል። ይሁን እንጂ ‘’ገና ላዩን ነው የነካነው፤ ያልሰራነው ይበልጣል’’ በማለት ዶ/ር አማኑኤል ገልፀዋል።

እነዚህን ሴቶች ለማገዝ ሰፊ ዕቅዶች እንዳሉ ተጠቁሟል።

ሀገሬ ቴቪ ያናገራት የጾታዊ ጥቃት ሰለባ የኾነችው ‘’ባርች’’ እና ሌሎች ሴቶች ከቁስላቸው መሻር እና እንደሁሉም ዜጋ መሥራት፣ ከቁዘማ መውጣትን እንደሚፈልጉ ነግረውናል።

ሁሉም ዜጋ ይተባበረን፤ መድሃኒት ይግዛልን፤ ከጎናችን መኾኑን ያሳየን የሚሉ መልዕክቶች ከእንባቸው ጋር አፍስሰዋል።

በበጣቢያው ሪፖርተር
2024-03-23