በትግራይ ክልል የእናቶች ሞት እና የኤች አይቪ ወረርሽኝ መጨመሩ ተገለፀ።
ከሁለት ዓመታት በላይ በጦርነት ውስጥ በቆየው የትግራይ ክልል የእናቶች እና ሕፃናት ሞት መጨመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
ከጦርነቱ በፊት ‘’የትግራይ ስታስቲክስ ኤጀንሲ’’ በሠራው ጥናት 100 ሺሕ በሕይወት ከሚወለዱ ሕፃናት 186 እናቶች ሕይወታቸውን ያጡ ነበር አሁን ላይ ይህ ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል ተብሏል።
በተለይ ከጦርነቱ በኋላ ‘’100 ሺሕ በሕይወት ከሚወለዱ ሕፃናት 840 እናቶች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ’’ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አማኑዔል ኀይለ ለጣቢያችን ተናግረዋል። ይህም ወደ አምስት ዕጥፍ የተጠጋ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ አዲስ ከሚወለዱ 1 ሺህ ሕፃናት ወደ 10 የሚኾኑት ይሞቱ ነበር፤ ከጦርነቱ በኋላ ግን ይህ ቁጥር ወደ 36 ማሻቀቡ ተገልጿል።
‘’ከአንድ ዓመት በታች እና ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ሕፃናትም ከጦርነቱ በፊት እና በኋላ ስታየው ሁለት እጥፍ ነው የኾነው’’ ብለዋል የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አማኑዔል ኀይለ።
በትግራይ ክልል በጤናው ዘርፍ ላለው ችግሮች ለየት ያለ ድጋፍ ያስፈል፤ እኛም እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ እንላለን ማለት አይደለም፣የሚቻለንን በሙሉ እናደርጋለን ሲሉ ገልፀዋል።
ከዚህ ባሻገር በክልሉ ያለው የምግብ እጥረት አሳሳቢ እንደኾነ ተናግረዋል።
‘’በቅርቡ በትግራይ ምስራቃዊ ዞን አጽቢ የሚባል ወረዳ ያለው የምግብ ዕጥረት እንዲታወቅ ከዩኒሴፍ ጋር በጋራ በመኾን ጥናት አካሔደናል።
በወረዳው 92 በመቶ ነፍሰጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ለምግብ ዕጥረት ተጋልጠዋል’’ ሲሉ ዶ/ር አማኑዔል ተናግረዋል። ‘’እኔ እንደዚህ ዐይነት ቁጥር ሰምቼ አላውቅም ከ 60 እስከ 70 በመቶ ነበር የሚያጋጥመው ይህም ቢኾን በጣም ከፍተኛ ነው የትም ቦታ የለም ብለዋል’’።
ሌላው ለዶ/ር አማኑዔል ያነሱት ጉዳይ በክልሉ ‘’በርካታ ሴቶች ላይ የደረሰ ፆታዊ ጥቃት’’ የኤች አይቪ ስርጭቱን እንዲጨምር ማድረጉን ነው።
ከጦርነቱ በፊት የበሽታው ስርጭት 1.43 በመቶ እየተጠጋ እንደነበር ነግረውናል። ወደ 46 ሺሕ የሚጠጉ የኤች አይ ቪ ኤድስ ሕሙማን እንደነበሩ እና ጦርነቱ ተጀምሮ በሰላም ስምምነቱ ከተቋጨ በኋላ ከነዚህ ታማሚዎች ወደ 10ሺሕ የሚጠጉት መጥፋታቸውን ዶ/ር አማኑዔል ነግረውናል።
አሁን ይህ ቁጥር ጠብቦ ወደ 34 ሺሕ የሚኾኑት የት እንዳሉ ማወቅ እንደተቻለ እና ወደ ሕክምና መመለሳቸው ተገልጿል። ቫይረሱን በቁጥጥር ውሏል ወይስ አልዋለም የሚለውን ለማረጋገጥ በመቐለ እና በአክሱም ከተማ ጥናት መጀመሩም ተነግሯል።
‘’በፊት ከነበረው ወሳኝ ለውጥ ግን አለ’’ ብለዋል ዶ/ር አማኑዔል ‘’ ጥናት ሳይደረግ ቁጥሩን መጥራት ሊከብድ ይችላል ነገር ግን [ኤች አይቪ] ከሚመረመሩ ሰዎች በደማቸው የሚገኘው ዝም ተብሎ የሚታለፍ ቁጥር አይደልም’’ ይላሉ የቢሮው ኃላፊ ‘’የጤና ዘርፍ ውስጥ እንዳለ ሰው ይሄ ወረርሽኝ ነው ብለን እናውጅ ነው ያልነው’’ ብለዋል።
በጦርነቱ ወቅት የደረሰው ጾታዊ ጥቃት አንዱ ምክንያት መኾኑ ተጠቅሷል። በትግራይ ክልል ‘’የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት እንደጨመረ’’ ጥያቄ የለውም ሲሉ ዶ/ር አማኑዔል ተናግረዋል።
ሰዉ ግንዛቤ እንዲኖረው ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰሩ መኾኑንም ገልፀዋል። ለዚህ በሽታ ተጋላጭ የኾኑትን፣ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ቶሎ በመመርመር ወደ ሕክምና ማስገባት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ተብሏል።
ጥናቶች ተጠንተው ትክክለኛው ውጤት ሲገኝም ይፋ እንደሚደረግ ዶ/ር አማኑዔል ተናግረዋል። በክልሉ ያለው የመድኃኒት ዕጥረት የኤች አይቪ ታማሚዎች ላይ ያደረሰው ተጽዕኖ ካለ እንዲነግሩን ጠይቀናቸው ነበር። በዚህ ላይ ያለው የመድኃኒት አቅርቦት ‘’ጥሩ’’ የሚባል እንደኾነ ገልፀዋል። ነገር ግን ከፍተኛ የማጓጓዣ ዕጥረት እንዳለ ተናግረዋል።
‘’በፊት ላይ ከአንድ ሳምንት ባነስ ጊዜ ውስጥ በክልሉ ላሉ የጤና የኤች አይ ቪ መድኃኒት ይሰራጭ ነበር አሁን ግን ከወር በላይ’’ እንደሚዘገይ ገልፀዋል። በትግራይ ክልል የመርመሪያ ኪት፣ የኮንዶም ዕጥረቶች እንደነበሩ፤ አሁን ላይ በመጠኑም ቢኾን መሻሻሎች እንዳሉ ተገልጿል።
በበጣቢያው ሪፖርተር
2024-03-28
