ዘመነ በተባለው ዓለም አሁን አሁን እየተለመደ ግዴታ እስከመምሰል ደርሷል።
በአደባባይ ጓደኛ ወይም ወዳጆች አልያም መንገደኛ ሰዎች ባሉበት የፍቅር አጋሮን የታገቢኛለሽ ወይ ጥያቄን መጠየቅ።
ታዲያ አሁንማ ባልተለመዱ መንገዶች ጭምር እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ሲቀርቡ መስማት የተለመደ ሆኗል።
እኛም ከወደ ደቡብ አፍሪካ የሰማነውን ግርምትን ያጫረብንን የታገቢኛለሽ ወይ ጥያቄ ልናጋራችሁ ወደድን።
አንድ ግለሰብ በፍቅር አጋሩ የአባቷ ቀብር ላይ በመገኘት ታገኒኛለሽ ወይ ሲል ጥያቄ ማቅረቡ በርካቶችን እያነጋገረ ይገኛል።
ለእንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ግዜ እና ቦታ ትልቅ ቁም ነገር ነው ባዮች ድርጊቱን እየኮነኑት ይገኛሉ።
ግለሰቡ በፍቅረኛው አባት የአስክሬን ሽኝት ላይ በመገኘት ወዳጅ ዘመድ ተሰብስቦ በሀዘን በተዋጠበት መድረክ የድምፅ ማጉያውን ይጨብጣል።
በመቀጠልም በሀዘንተኛዋ የፍቅር አጋሩ ስር ተንበርክኮ አግቢኝ ብሏታል።
አባቷን በሞት የተነጠቀችው የወጣቱ የፍቅር አጋርም በእሷ እና በአባቷ የአስክሬን ሳጥን መሀል ለቆመው ወጣት ከለቅሶዋ ሳታባራ የሚሆነውን ስትመለከት ነበር።
ወጣቷ ለግለሰቡ ጥያቄ ምንም አይነት ምላሽ የሰጠች ባትመስልም ሰውየው ግን በሀዝንተኛዋ ጣቶች ላይ ያለ ማንም ከልካይ የቃልኪዳን ቀለበቱን አኑሯል።
በድርጊቱ የተቆጡ በርካቶች እንዴት እንዲህ ይደረጋል እያሉም ይገኛሉ።
በተለይ ግለሰቡ እንደማንኛውም አይነት ሰው ሳይሆን የሀይማኖት አስተማሪ ነው መባሉ ደግሞ የበለጠ ድርጊቱን በሚያወግዙ ሰዎች ዘንድ እንዲተች አድርጎታል።
የግለሰቡን ድርጊት በርካቶች ቢቃወሙም በዛው መጠን ደግሞ ደግ አደረክ የአባቷ ምትክ ለመሆን በአባቷ ቀብር ላይ ቃልኪዳን ማሰርክ የፍቅርክን ጥልቀት የሚያሳይ ነው እና አበጀክ ብለውታል።
ልቅሶ እና ሳቅ አንድ ላይ ይለዋል ይህ ነው።
በሳምሶን ገድሉ
2022-05-16
